የአፈር ለምነትና የማደበሪያ አጠቃቀም ምክረ ሃሳብ ጥናት በዘርፉ የሚታየውን ችግር እንደሚፈታ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የአፈር ለምነትና የማደበሪያ አጠቃቀም ምክረ ሃሳብ ጥናት በዘርፉ የሚታየውን ችግር እንደሚፈታ ተገለጸ
ጋምቤላ ሐምሌ 3/2011 ኢዜአ በሀገር አቀፍ ደረጃ የተካሄደው የአፈር ለምነትና የማደበሪያ አጠቃቀም ምክረ ሃሳብ ጥናት በዘርፉ የሚታየውን ችግር የሚፈታ መሆኑ የኢትዮጵያ ግብርና ትራንሰፎርሜሽን ኤጀንሲ አስታወቀ። ኤጀንሲው የጋምቤላ ክልልን የአፈር ለምነትና የማደበሪያ አጠቀቀም ምክረ ሃሳብ ጥናት ካርታ ለክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስርክቧል። በኤጀንሲው የአፈር ሀብት መረጃ ስርዓት ቡድን መሪ አቶ ተገባሩ በለጠ በካርታ ርክክቡ ወቅት እንደገለጹት ሀገር አቀፉ ጥናት ሳይንሳዊ የማደበሪያ አጠቀቀም ስርዓትን ለመዘርጋት ነው። ቀደም ሲል በአፈር ውስጥ የተጓደሉ ንጥረ ነገሮች ሳይጠኑ ዳፕና ዩሪያ የተባሉት የማደበሪያ ዓይነቶች በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ስራ ላይ ሲውሉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። በግምታዊ የማደበሪያ አጠቀቀምን ተከትሎ አርሶ አደሩ በተፈለገው መጠን ምርታማ ሳይሆን ቆይቷል። ችግሩን ለማቃለል በሀገር አቀፍ ደረጃ በ728 ወረዳዎች ላይ ከ80 ሺህ በላይ የአፈር ናሙናዎች ተሰብስበው የቤተሙከራ ምርመራ መደረጉን አስረድተዋል። በጋምቤላ ክልል በተካሄደው የአፈር ለምነትና የማደበሪያ አጠቀቀም ጥናት ቦሮንና ዚንክ የተባሉት ጨምሮ የስድስት ንጥር ነገሮች እጥርት እንዳለ መለየቱን ጠቁመዋል። በጥናቱ መሰረተ ካርቦን፣ ከዚንክና ከናይተሮጅን ጋር አስር የማዳበሪያ ዓይነቶች እንደሚያስፈልጉ አመላክተዋል። የጋምቤላ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ዶክትር ሎው ኡቡፕ የጥናቱን ካርታ በተረከቡበት ወቅት "በክልሉ ቀደም ሲል በተለምዶ መሬቱ ድንግል ነው በሚል አርሶ አደሩ የማዳበሪያ ግብዓትን ሳይጠቀም ቆይቷል" ብለዋል። በተካሄደው የአፈር ለምነትና የማዳበሪያ አጠቀቀም ጥናት የክልሉ አፈር አሲደማና የተለያዩ ሰው ሰራሽ የማደበሪያ ዓይነቶች እንደሚያስፈልጉት መረጋጡን አስታውቀዋል። በሀገር አቀፉ ጥናት የተለዩትን የማደበሪያ ዓይነቶች ወደ ክልሉ በማስገባት ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።