ቀጥታ፡

ኮሌጁ ከሁለት ሺህ በላይ እጩ መኮንኖችንና ምልምል ፖሊሶችን አስመረቀ

ደብረ ማርቆስ ሰኔ 3/2010 በደብረ ማርቆስ ከተማ የሚገኘው የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ ያሰለጠናቸውን ሁለት ሺህ 70 እጩ መኮንኖችንና ምልምል ፖሊሶችን አስመረቀ፡፡ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ረዳት ኮሚሽነር ጥበበ ኃይሉ ትናንት በተካሄደው የምረቃ ስነ ስርዓት ወቅት እንደገለጹት ኮሚሽኑ ብቁ ምልምል የፖሊስ አባላትንና መኮንኖችን በማሰልጠን የአካባቢውን የጸጥታ ኃይል ክፍተት እየሞላ ይገኛል። በቀጣይም የህዝብ ደህንነትን በመጠበቅ በቅንነትና በታማኝነት የሚያገለግል የፖሊስ አባል ለማፍራት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራም አመልክተዋል። የክልሉ አስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አዘዝ ዋሴ በበኩላቸው ሰልጣኞቹ በቆይታቸው ያገኙትን እውቀትና ክህሎት ተጠቅመው ከህዝብ ጋር በመሆን ወንጀል ከመሰራቱ በፊት መከላከልና ህግን ማስከበር እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል። ለጸጥታ ስጋት የሆኑትን የኃይማኖት አክራሪነት፣ ሽብርተኝነት፣ ህገወጥ የመሳሪያ እና የሰዎች ዝውውር ወንጀሎችን ተከታትሎ ማምከን እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡ የኮሌጁ ትምህርትና ስልጠና ክፍል ተወካይ ኮማንደር አበበ ደለለ በበኩላቸው ሰልጣኞቹ ከአምስት እስከ 27 ወራት በትምህርት ላይ እንደቆዩ ተናግረው ከመካከላቸውም አንድ ሺህ 960 እጩ መኮንኖች እና ቀሪዎቹ መደበኛ ምልምል ፖሊሶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከጠቅላላ ተመራቂዎች ውስጥም 156 ሴቶች ሲሆኑ ዘጠኝ ሰልጣኞች ደግሞ ከቤንሻንጉልጉሙዝ ክልል የመጡ ናቸው፡፡ ሰልጣኞች በቆይታቸው በልዩ ልዩ ፖሊሳዊ ሙያ የንድፍ ሀሳብና የተግባር ትምህርት ተከተትለው ያጠናቀቁ ናቸው ተብሏል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል ረዳት ኢንስፔክተር ባለው አዳሙ በሰጠው አስተያየት በስልጠናው ያገኘውን እውቀት ተግባር ላይ በማዋል የተጣለበትን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል። ኮንስታብል መሀመድ ሳይድ በበኩሉ "ህዝብን በታማኝነት እና በቅንነት እንዳገለግል የሚያስችል ስልጠና በማግኘቴ ተደስቻለሁ" ብለዋል። የአማራ ፖሊስ ኮሌጅ ከተቋቋመት ጊዜ ጀምሮ 38 ሺህ ያህል የፖሊስ አባላት ማሰልጠኑን በምረቃው ስነስርዓት ወቅት ተገልጿል፡፡        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም