ቀጥታ፡

የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማትን አቅም ለማሳደግ የሚያግዝ ሲፋ የተሰኘ መርሃ-ግብር ይፋ ሆነ

ሐምሌ 3/2011 የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማትን አቅም ለማጎልበት የሚያስችል የክህሎት ኢንሼቲቭ ለአፍሪካ (ሲፋ) የተሰኘ መርሃ-ግብር ይፋ ሆነ። ሲፋ (Skills Initiative for Africa) መርሃ-ግብርን በዛሬው እለት በኢትዮጵያ ለመጀመር የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚኒስትር፣ በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር፣ የአፍሪካ ህብረት የልማት ኤጀንሲ ኃላፊና ሌሎች በተገኙበት ይፋ ሆኗል። በአፍሪካ ህብረት የልማት ኤጀንሲ አስተባባሪነት በተለይም በጀርመን መንግስት የገንዘብ ድጋፍ የሚከወን ሲሆን ከአውሮፓ ህብረት ድጋፍ ያገኛል። ተቋማት በሚያቀርቡት የመነሻ ሃሳብ መሰረት እስከ ሶስት ሚሊዮን ዩሮ የሚያገኙበትና ቀደም ሲል በሰባት የአፍሪካ አገራት በሙከራ ደረጃ ይተገበር የነበረው መርሃ--ግብር ኢትዮጵያን በስምንተኛነት አካትቷል። መርሃ-ግብሩ ይፋ ሲሆን የኤጀንሲው የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት መርሃ-ግብር ኃላፊ ሚስ ፋቲ ኒዝ ሀሰን እንዳሉት አዲስ አጋርነት ለአፍሪካ ልማት በ2015 ያስጠናው ጥናት በ2030 በአህጉሪቱ 440 ሚሊዮን ወጣቶች የስራ ገበያውን እንደሚቀላቀሉ ያመለክታል። እነዚህ ወጣቶች በሚገባ ከተዘጋጁና ካስተማርናቸው እንዲሁም እድሎችን ካገኙ አጀንዳ 2063ን ለማሳካት የሚያስችሉና አህጉሪቱን የዓለም  አቀፍ የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ እንደሚሆኑም ይናገራሉ። የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ወጣቶችን ለቅጥርና ለስራ ፈጠራ ብቁ የሚያደርጉ መሆናቸውንም ተናግረዋል። የተቋማቱን የትምህርትና የስልጠና ስርዓት በማሻሻል የእውቀት፣ ምርምር፣ ክህሎት፣ ፈጠራና የፈጠራ ችሎታን በማዳበር የአፍሪካና የወጣቶቿን ዕድል መወሰን ያስችላልም ብለዋል። የአፍሪካ ህብረት የቴክኒክና ትምህርት ተቋማትን አቅም ለማሻሻል የወጣቶችን ክህሎትን ለማዳበርና የስራ እድል እንዲያገኙ ለማስቻል አህጉራዊ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ ቢያዘጋጅም የብቁ መምህራን እጥረት የመሰረተ-ልማት አለመሟላትና የመሳሰሉት ስትራቴጂው እንዳይሳካ ማነቆ ሆነዋል ነው ያሉት። መርሃ-ግብሩ ይህን ችግር ለመቅረፍ ተቋማት በሚያቀርቡት መነሻ ሃሳብ መሰረት የስልጠና የቁሳቁስና የግንባታንም ጭምር ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያስችልና ችግሩን የሚፈታ መሆኑን በመግለፅ። የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማርያም በበኩላቸው መርሃ-ግብሩ ቴክኒክና ሙያ ስልጠናና ትምህርት ተቋማት አቅማቸውን እንዲያጠነክሩና ብቁ ሰልጣኞችን ለማፍራት የሚያስችል ነው ብለዋል። መርሃ-ግብሩ ተቋማቱ የሚሰጡት ስልጠና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ከስርዓተ ትምህርት ጀምሮ ግብዓትን ማሟላትና አሰልጣኞችንም ማብቃትን የሚያካትት መሆኑ ሰልጣኞች ጥራቱን የጠበቀ ስልጠና እንዲያገኙና በክህሎትና ሙያ የበለፀጉ እንዲሆኑ ያደርጋል ብለዋል። ተቋማት በሚያቀርቡት መነሻ ሃሳብ ተወዳድረው የሚያገኙት እድል መሆኑን ገለፀው ሚኒስቴሩምጥራት ያለው የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስርዓት መዘርጋት ለኢንዱስትሪው ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል ነውና የሀገሪቱን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ለማሳካት ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል። ሚኒስቴሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በዘርፉ እየገጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን የገለፁት ፕሮፌሰር ሂሩት መርሃ-ግብሩም ለዚህ እገዛ እንዳለው አስረድተዋል። መርሃ-ግብሩ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ካሜሩን፣ ኬንያ፣ ቱኒዚያ፣ ቶጎ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ናይጄሪያና ጋና የሚተገበር ሲሆን በሚያቀርቡት የመነሻ ሃሳብ መሰረት እስከ ሶስት ሚሊዮን ዩሮ የሚደርስ የቁሳቁስ ድጋፍ፣ የመምህራን ስልጠና፣ የአቅም ግንባታ ድጋፍ ያገኛሉ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም