የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አማረ አምሳሉ ክስ ተመሰረተባቸው - ኢዜአ አማርኛ
የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አማረ አምሳሉ ክስ ተመሰረተባቸው
አዲስ አበባ ኢዜአ ሃምሌ 3/2011የፌዴራሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በቀድሞ የኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አማረ አምሳሉ ላይ ክስ መሰረተ። አቃቤ ሕግ አቶ አማረ አምሳሉን ጨምሮ በሌሎች 10 የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ላይ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ክስ መስርቶባቸዋል። በዚሁ መዝገብ ክስ የተመሰረተባቸው 1ኛ አቶ አማረ አምሳሉ፣ 2ኛ አቶ ወልደጊዮርጊስ ወልዱ፣ 3ኛ አቶ ኢሳያስ ዳኘው፣ 4ኛ አቶ አብዱልሃፊዝ አህመድ፣ 5ኛ አቶ ማስረሻ ጥላሁን፣ 6ኛ አቶ ሰይፈ ኃይለስላሴ፣ 7ኛ አቶ ፀጋየ መኮንን፣ 8ኛ አቶ አይተንፍስ ወርቁ፣ 9ኛ አቶ ጌታሁን ያሲን እና 10ኛ አቶ ሳሙኤል ፈጠነ ናቸው። ተከሳሾቹ ስልጣንን ያለአግባብ በመገልገል እንዲሁም የመንግስትን ስራ በማያመች አኳኋን በመምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ነው ክስ የተመሰረተባቸው። ከ259 ሚሊዮን ብር በላይ በኢትዮ ቴሌኮም፣ በህዝብና በመንግስት ላይ ጉዳት በማድረስ ወንጀልም መጠርጠራቸውን የክስ መዝገቡ ያመለክታል። በሶማሌ ክልል የሞባይል ማስፋፊያ ግንባታ የአገልግሎት ግዥ ውል በሚከናወንበት ወቅት ለራሳቸው ብሎም ለብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ጥቅም ለማስገኘት በማሰብ የኢትዮ ቴሌኮምን የግዥ መመሪያ ብሎም የመንግስትን የግዥ መመሪያ ተላልፈው ፈፅመዋል ተብሏል። ለዚሁ ግንባታ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የሲቪል ስራን ለማከናወን ያቀረበውን የ99 ሚሊዮን 905 ሺህ 731 ብር ዋጋ ወደ ጎን በመተው ሜቴክ ያለውድድር በ321 ሚሊዮን 710 ሺህ 424 ብር እንዲሰራ አድርገዋል። በዚህምለሜቴክ 221 ሚሊዮን 804 ሺህ 693 ብርተጨማሪእንዲያገኝመደረጉበክሱተብራርቷል። በኢትዮ ቴሌኮም የግንባታ ርክክብ ዝርዝር ስፔስፊኬሽንን መሰረት ሳይደረግና 51 ፕሮጀክቶች ሳይጠናቀቁ ርክክብ በመደረጉ ከ69 ሚሊዮን ብር በላይ ከደንብና መመሪያ ውጭ እንዲከፈልም ተደርጓል። በተጨማሪ 161 የመፀዳጃ ቤቶችና 161 የጥበቃ ቤቶች የግንባታ ሂደታቸው ሳይጠናቀቅ እንደተጠናቀቁ በማስመስል ርክክብ በማድረግ በአጠቃላይ ከ295 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ በከባድ የሙስና ወንጀል መጠርጠራቸው መሆኑ ተገልጿል። አምስተኛ ተከሳሽ አቶ ማስረሻ ጥላሁን እና ስምንተኛ ተከሳሽ አቶ አይተንፍስ ወርቁ በትላንትናው እለት ክሱ የተነበበላቸው ሲሆን "ክሱን ተረድተነዋል" በማለት የዋስትና መብት እንዲከበርላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡ ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ተከሳሾች የተጠረጠሩበት ወንጀል ከ10 ዓመት በላይ የሚያስቀጣቸው ከባድ የሙስና ወንጀል በመሆኑ የዋስትና መብት እንደይሰጣቸው በማለት ተከራክሯል። ፍርድ ቤቱም ተከሳሾች ከጠበቆቻቸው ጋር መክረው የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡