ቀጥታ፡

ህገ-መንግስቱ ካልተሻሻለ በኢትዮጵያ የሚነሱ ክልል የመሆን ጥያቄዎችን መፍታት አዳጋች ነው ተባለ

ሐምሌ 2 / 2011( ኢዜ አ) በኢትዮጵያ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ለማስከበርና የ'ክልል ልሁን' ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመመለስ ህገ-መንግስቱን ማሻሻል ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑ ተገለጸ። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፌዴራሊዝም ጥናት ማዕከልና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ''በኢትዮጵያ የክልልነት ጥያቄ ህገ-መንግስታዊና ፖለቲካዊ አንድምታዎች'' በሚል ርዕስ በጋራ ያዘጋጁት የምክክር መድረክ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በዚሁ ጊዜ በአገሪቷ አንዳንድ አካባቢዎች የሚነሱ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎችን በአግባቡ ለመመለስ በቅድሚያ ህገ-መንግስቱን ማሻሻል ተገቢ መሆኑ ነው የተገለጸው። የዜጎች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ዓለምአቀፋዊ መሆኑንና በኢትዮጵያም ከረጅም ዓመታት ጀምሮ ዜጎች በተለያየ ጊዜ ጥያቄውን ያነሱ እንደነበር ነው በመድረኩ ተሳታፊዎች የተነሳው። ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን ስልጣን እንዳላቸው በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 39  ላይ ተቀምጧል። ይሁንና አፈጻጸሙ ላይ ክፍተት በመኖሩ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚነሱ የክልልነት ጥያቄዎች በወቅቱ ምላሽ አለማግኘታቸውን አንስተዋል። ከፀደቀ 25 ዓመታትን ያስቆጠረው የአገሪቷ ህገ-መንግስት የህጎች ሁሉ የበላይ እንደመሆኑ አሁን ካለው የአገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ የተጣጣመና የህዝቦችን ጥያቄ በማያሻማ መልኩ መመለስ እንዲችል መሻሻል አለበት ተብሏል በመድረኩ። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፌዴራሊዝም ጥናት ማዕከልና የህግና አስተዳደር ትምህርት ክፍል የመጡ በመድረኩ የመነሻ ጽሁፍ ያቀረቡ ምሁራንም  የአገሪቷ ህገ-መንግስት ሲፀድቅ ህዝቡን በአግባቡ ካለማወያየቱ ባለፈ አሁን አገሪቷ ከደረሰችበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ሊሻሻል ይገባል ብለዋል። በሌሎች አገሮች የክልልነት ጥያቄዎች በምን አይነት መልኩ እየተመለሱ እንደሆነም የህንድና የስዊዘርላንድን ተሞክሮ መነሻ በማድረግ ውይይት ተደርጎበታል። በስዊዘርላንድ የምትገኝ 'ጁራ' የተባለች ክልል ራሷን ችላ ክልል ከመሆኗ በፊት በተለያዩ እርከኖች ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ውይይት ማድረጋቸውንና የክልልነት ጥያቄዋን ለመመለስም ረጅም ዓመታት መፍጀቱን ለአብነት አንስተዋል። በሌላ በኩል በህንድ ህገ-መንግስት ክልል መመስረት የሚችለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን ነው የተጠቀሰው። ኢትዮጵያም እስካሁን ባለው ሂደት የክልልነት ጥያቄን እንዴት ማስተናገድ እንደሚቻል በቂ ልምድ የሌላት በመሆኑ የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው አገሮች ልምድ መቅሰም እንዳለባት ምሁራኑ ተናግረዋል። ይሁንና የክልልነት ጥያቄዎችን ለመመለስ በቅድሚያ ህገ -መንግስቱ ላይ መሻሻል ያለባቸውን ድንጋጌዎች ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት ተገቢ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተታል።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም