በሰበታ ከተማ የሚገኙ ባለኃብቶች ያሉባቸው ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
በሰበታ ከተማ የሚገኙ ባለኃብቶች ያሉባቸው ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠየቁ
ሐምሌ 2/2011 (ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ሰበታ ከተማ የሚገኙ ባለኃብቶች በሥራቸው እያጋጠማቸው ያለውን ችግር መንግስት እንዲቀርፍላቸው ጠየቁ። የክልሉ መንግስት በበኩሉ ባለኃብቶች የሚገጥማቸውን ችግር መፍታት እንዲቻል የጀመረውን ጥናት በማጠናቀቅ ላይ ነው፤ ችግሮቹን የመፍታት እርምጃ ይወሰዳል ሲል ገልጿል። በክልሉ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያለበትን ደረጃ በመገምገም ሊወሰዱ የሚገባቸውን የማጠናከሪያ እርምጃዎች መቃኘትን ዓላማው ያደረገ ጉብኝት ዛሬ በክልሉ ዘጠኝ ከተሞች ተካሂዷል። ጉብኝቱ በክልሉ ያለውን ኢንቨስትመንት የበለጠ ለማነቃቃትና መንግስት መወጣት ያለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ለማድረግ እንደዚሁም በቀጣይነት የሚነሱ ችግሮችን መፍታት የሚቻልበትን መንገድ መዘየድ ነው። በዚህም መሰረት በኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ የተመራ የክልሉ መንግስት የልዕካን ቡድን በሰበታ ከተማ የሚገኙ ፋብሪካዎችን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝቷል። የልኡካን ቡድኑ ከጎበኛቸው መካከል ቢ ኤም ኢ ቲ የኬብል ማምረቻ፣ የአርባ ምንጭ ጨርቃ ጨርቅ እና የዋን ውሃ ፋብሪካዎች ይገኙበታል። በዚሁ ወቅትም ባለኃብቱ እና የክልሉ አመራር አካላት ውይይት ያካሄዱ ሲሆን በአጠቃላይ በክልሉ ያሉት ፋብሪካዎችን ችግር ለመፍታት መንግስት በተለየ ሁኔታ እየተሰራ መሆኑ በውይይቱ ላይ ተገልጿል። የግሉ ዘርፍም ሰፊ የሥራ እድል በመፍጠርና የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ረገድ የሚያበረታታ ተግባር እያከናወነ መሆኑም ተወስቷል። ሆኖም የውጭ ምንዛሬ፣ የማስፋፊያ ቦታ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እና ተያያዥ ችግሮች እንዲፈቱላቸው ባለኃብቱ በዚሁ ወቅት ጠይቀዋል። በእነዚህ ችግሮች የተነሳ በሙሉ አቅማቸው ምርት እየሰሩ እንዳልሆነ ነው ባለኃብቶቹ የተናግሩት። የልኡካን ቡድኑ መሪ አቶ አዲሱ አረጋ በበከኩላቸው መንግስት በክልሉ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል ጥናት እያካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል። ጥናቱ በቅርብ እንደሚጠናቀቅና የክልሉ መሪዎች በውጤቱ ላይ ከበላኃብቶች ጋር ውይይት በማካሄድ ለችግሮቹ መፍትሄ እንደሚበጅ አረጋግጠዋል። ከዚሁ ጋርም ባለኃብቶቹ በሙሉ አቅማቸው መስራት የሚያስችላቸውን ድጋፍ የክልሉ መንግስት የሚያደርግ መሆኑንም አቶ አዲሱ ገልፀዋል። ከቀረጥና ከፖሊሲ ጋር ተያይዘው ያሉትን ተግዳሮቶች መፍታት ይቻል ዘንድም የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት በቀጣይ ውይይት እንደሚካሄድም ተናግረዋል። የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት የግሉን ዘርፍ በማበረታታትና በመደገፍ ክልሉን የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ማእከል ለማድረግ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል። መንግስት ባለኃብቶችን ለመደገፍ ከምንጊዜውም በላይ በቁርጠኝነት እየሰራ ነው፣ነገር ግን መሬት በመውሰድ ላልተገባ ተግባር በሚያውሉ ላይ መንግስት የማስተካከያ እርምጃ ይወስዳል ሲሉ አቶ አዲሱ አመልክተዋል። ባለኃብቶች የሚያነሱት ጥያቄ በሂደት እንደሚፈታ ገልጸው በክልል ደረጃ የማይመለሱ ችግሮችን ደግሞ ከሚመለከተው አካላት ጋር ለመፍታት እንደሚሰራም ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ ሆን ብለው የኢንዱስትሪውን ሰላም ለማስተጓጎል በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ መንግስት ህግ የማስከበር እርምጃ እንደሚወስድ አቶ አዲሱ አስገንዝበዋል። በየደረጃው ያሉት የመንግስት ኃላፊዎች ባለኃብቱ የሚያነሳውን ችግር ለመፍታት በሚያስችል መልኩ በቅርበት የሚሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። በጉብኝቱ ወቅት በተለያየ የኢንቨስትመንት መስክ የተማሩ ባለኃብቶች በውላቸው መሰረት ሥራቸውን በማከናወን የሥራ እድል መፍጠርንና የክልሉን ገቢ ማሳደግን ጨምሮ የክልሉንና የአገሪቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ተመልክቷል።