መንግሥት ለአካል ጉዳተኞች ጥያቄዎችን ለመመለስ ትኩረት መስጠቱን ሚኒስቴሩ ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት ለአካል ጉዳተኞች ጥያቄዎችን ለመመለስ ትኩረት መስጠቱን ሚኒስቴሩ ገለጹ
አዳማ ሐምሌ 2/2011 ( ኢዜ አ) መንግሥት የአካል ጉዳተኞች ጥያቄዎችን ለመመለስ ትኩረት መስጠቱን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቁ። የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኀበራት ፌዴሬሽን 21ኛ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔውን ዛሬ በአዳማ ከተማ አካሂዷል። ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ጌታሁን አብዲሳ በጉባዔው ላይ እንደተናገሩት መንግሥት የአካል ጉዳተኞችን ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መብትን መሠረት አድርጎ በመሥራት ላይ ነው። በዚህም ፖሊሲዎችን ከመቅረፅና ሕግጋትን ከማውጣት ባለፈ፤አስፈጻሚ አካላትን በማደራጀት በአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ዙሪያ ድርሻ ያላቸውን አካላት በማስተባበር ጥያቄዎቻቸውን ለመመለስ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል። በተለይም ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ፈጥኖ በመቀበልና በመተግበር መንግሥት ''ፋና ወጊ'' ተግባራት ማከናወኑን አቶ ጌታሁን አስረድተዋል። ነገር ግን የአካል ጉዳተኞች ችግር በባህሪው የተወሳሰበና ልዩ ጥረትን ስለሚጠይቅ ሁሉም አካላት እንዲረባረቡ አሳስበዋል። ''ለውጡ ለኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች መብትና ጥቅም የሚሰራበት መልካም ዕድል ይዞ መጥቷል'' ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ዕድሉን እንዲጠቁሙበት ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል። የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማኀበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ ፌዴሬሽኑ ከመንግሥት ጋር በቅርበት በመስራት አካል ጉዳተኝነትን የሚመለከቱ የልማት እንቅስቃሴዎች የሚሻሻሉበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት የሶስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ አዘጋጅቶ በትግበራ ላይ እንደሚገኝ ያመለከቱት ዋና ዳይሬክተሩ በተለይ አካል ጉዳተኞችን የሚስተዋሉ የመረጃ መዋዠቅና ክፍተት ለማስወገድ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በ3 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወጪ የሴቶች፣ሕፃናትና ወጣት አካል ጉዳተኞችን የልማት ተጠቃሚነት ለማሻሻል ጥረት መደረጉን አመልክተዋል። የፌዴሬሽኑ የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ውስጥ አቅም ለማሳደግ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ሀብት ለማሰባሰብ እንደሚሰራ ገልጸዋል። የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጅማ ዲልቦ በበኩላቸው የአካል ጉዳተኞችን መብትና ጥቅም ለማስከበር በመንግሥት አቅም ብቻ ስለማይቻል የሲቪል ማህበራት ተሳትፎአቸውን እንዲያሳድጉ ጠይቀዋል። ኤጀንሲው ለሁለንተናዊ ተሳትፎአቸው መዳበር የሚያደርገውን ጥረት እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። በኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ከሕዝቡ 18 በመቶ እንደሚሸፍኑ መረጃዎች ያመለክታሉ።