በጎንደር ከተማ ትላንት አጋጥሞ የነበረው የጸጥታ ችግር መፈታቱን ፖሊስ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ከተማ ትላንት አጋጥሞ የነበረው የጸጥታ ችግር መፈታቱን ፖሊስ አስታወቀ
ሀምሌ 2/2011 ( ኢዜ አ) ከፋሲል ከነማ ቡድን ደጋፊዎች ጋር በተያያዘ በጎንደር ከተማ ትላንት ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር ወደ ተረጋጋ ሁኔታ መመለሱን የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡ መምሪያው ለኢዜአ እንደገለጸው ባለፈው እሁድ ፋሲል ከነማ ከስሑል ሽሬ ጋር የነበረውን የመጨረሻ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ውጤትን ተከትሎ በአንዳንድ የክለቡ ደጋፊዎች አማካኝነት በጎንደር ከተማ ግጭት ተከስቶ ነበር ። የመመሪያው የህዝብ ግንኙነት ኦፊሰር ኮማንደር ማረልኝ ወንድሙ እንዳሉት ግጭቱን ተከትሎ በነበረው አለመረጋጋት ትናንት ከሰባት ሰዓት በኋላ በከተማዋ የሚገኙ አንዳንድ የንግድ ተቋማትና ባንኮች ተዘግተው ነበር። ሁሉም የፀጥታ አካልና የከተማው ህዝብ ና የከተማው የማረጋጋት ሥራ ጸጥታወው በመረጋጋቱ ዛሬ ሁሉም መደበኛ ስራቸውን እያከናወኑ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡ እንደ ኮማንደሩ ገለፃ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ አለመግባባቶችን ምክንያት በማድረግ የህዝቡን ሰላም መንሳት ተገቢ አይደለም። በግጭቱም አንዳንድ የንግድ ተቋማት ላይ ጉዳት መድረሱን የገለጹት ኮማንደር ማረልኝ የደረሰውን የጉዳት መጠን የማጣራት ስራ መጀመሩን ጠቁመ በጥፋቱ የተሳተፉ ግለሰቦችም በቀጣይ የማጣራት ስራ ከተከናወነ በኋላ በህግ ተጠያቂ እንደሚደረጉ ተናግረዋል። አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው እንደተናገሩት ሁሉም የፀጥታ አካላት ተቀናጅተው የከተማዋን ሰላም ፈጥነው መመለሳቸው በፀጥታ አካሉ ያላቸውን እምነት ከፍ አድርጎታል። ከከተማው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ጥሩወርቅ ዋኘው እንዳሉት ክልሉ ወቅታዊ ችግር እያለበት ይህ ግርግር መፈጠሩ እጅጉን የሚያሳዝን ነው። ወጣቱ ኃይል ለሀገሪቱ ሊጠቅም በሚችል ተግባር እንጂ ወደ ጥፋት በሚወስድ ድርጊት ላይ ጉልበትና ጊዜውን ማባከን እንደሌለበትም መክረዋል። በጸጥታ ኃይሉ ርብርብ ከተማቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈጥኖ ሰላሙ በመመለሱ ለጸጥታ ኃይሉ ያላቸውን አድንቆትም ተናግረዋል። ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ ሙሉቀን ጥጋቡ በበኩላቸው እንዳሉት ስፖርትን ለብሔራዊ መግባባትና ገፅታ ግንባታ እንጂ ለጥላቻና ለእርስ በእርስ ግጭት ማዋል ከስፖርቱ ዓላማና ስነ-ምግባር ውጭ በመሆኑ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ሊያወግዘው ይገባል፡፡ “በስፖርት ሜዳ አለመግባባት ሊኖር ይችላል ነገር ግን ይህን አለመግባባት በማክረር ሌላ መልክ እንዲይዝ የሚያደርጉ ግለሰቦችና ቡድኖች ተጠያቂ መሆን አለባቸው” ብለዋል። የከተማዋን ሰላምና ፀጥታ በማስጠበበቅ በኩልም ቀጣይ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን ሆነው እንደሚሰሩ አስተያየት ሰጪዎቹ መናገራቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡