የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እይታ - ኢዜአ አማርኛ
የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እይታ
ምናሴ ያደሳ(ኢዜአ) የማህበራዊ ሚዲያ መስፋፋት በአስተሳሰብ በላቁና በአኗኗር ዘዬ በሰለጠኑ ያደጉ ሀገራት ህዝቦች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ልማት ዘንድ ገንቢ ሚና እያበረከተ ይገኛል ። ለፈጣንና ፍትሀዊ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች፣ ለውጤታማ የንግድና የቢዝነስ ሥራዎች ጠቀሜታው የጎላ ነው - ማህበራዊ ሚዲያ ። በዓለማችን ከጫፍ እስከ ጫፍ ተመሳሳይ ሙያና እውቀት ያላቸው ግለሰቦች በአንድ ጊዜ ተገናኝተው ተጨማሪ ዕውቀት እንዲቀስሙና ልምድ እንዲለዋወጡ በማድረግ በኩልም ማህበራዊ ሚዲያው አስተዋፅኦው ከፍተኛ ነው። በማሀበራዊ ሚዲያ የተጀመረ ግንኙነትና ወዳጅነትም ወደ ፍቅር ተቀይሮ በአንድ ሀገርም ይሁን በተለያዩ ክፍለ አለማት የሚገኙ ሰዎች ተቀራርበው ሦስት ጉልቻ እስከመመስረትና ልጅ ወልደው እስከ መሳም ሲደርሱ የታዘብንም አንጠፋም። በአንጻሩ በዕድገት ወደኋላ በቀሩ ሀገሮች ከላይ የተጠቀሱት የማህበራዊ ሚዲያ ጠቀሜታዎች በተቃራኒው ሆኖ ይስተዋላል። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ያላደጉ ሀገራት የሚገኙ ዜጎች ማሀበራዊ ሚዲያዎችን ከፍቅር ይልቅ ለጥላቻ፣ ከትዳር ይልቅ ለፍቺ ፣ ከልማትና ዕድገት ይልቅ ጥፋትን ለመስበክ ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። ከሰላምና አብሮነት ይልቅ ጦርነትና መለያየትን በማቀንቀን ላይ አተኩረው ሲባዘኑ እየታዘብን ነው። ባደጉትና ባላደጉት ሀገራት መካከል ለምን ይሄን ያህል ልዩነት ተፈጠረ ? ይሄ የሚያሳየን በማሀበራዊ ሚዲያዎች ምንነትና በመረጃ አጠቃቀም ላይ ሰፊ የግንዛቤ ልዩነት በመኖሩ ነው ። የመቱ ዩኒቨርሲቲ ሰሞኑን ተማሪዎቹን ሲያስመርቅ በተገኘሁበት ወቅት በዚህ ዙሪያ በተመራቂ ተማሪዎች አዕምሮ ውስጥ ያለን ነገር ለማወቅ ፈለግኩኝ። በሀገራችን ዜጎች በተለይም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ የታዘቡትን ችግሮችና የመፍትሄ ሀሳቦች እንዲሁም ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ለቀሩት ሌሎች ተማሪዎች የሚያስተላለፉት መልዕክት ካለ ብዬ ከእነሱ ጋር እጭር ቆይታ አደረኩ። ተማሪ ገመዳ ዋቅጋሪ ከዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ ተማሪዎች ከፍተኛ ነጥብ በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ ነው። ገመዳ እንዳጫወተኝ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ አልፎ አልፎ ሲከሰቱ የነበሩ ግጭቶችና ይህንኑ ተከትሎ የሚከሰተው የትምህርት መስተጓጎል ከባድ ፈተናና ጭንቀት ውስጥ አስገብቶት ነበር። ሆኖም ግን ይህንን ሁሉ ተቋቁሞ 3 ነጥብ 99 በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል። በተለይ የአዕምሮ ንቃተ ህሊናውን በመጠቀም በማህበራዊ ሚዲያ ለሚሰራጩ ሀሰተኛና የጥላቻ ንግግሮች ጆሮ ሳይሰጥ ባያልፍ ኖሮ ለዚህ ውጤት መብቃት ከባድ ይሆንበት እንደነበር ነው የነገረኝ። ተማሪው እንዳለው ከሆነ በማህበራዊ ሚዲያዎች ሆን ብለው የሚሰራጩ ሀሰተኛና የጥላቻ መልዕክቶች በተማሪዎች መካከል ግጭቶችን ከመፍጠር ባለፈ ተማሪዎች ሀሰተኛ መረጃዎቹን በመከታተል ጊዜያቸውን ስለሚያጠፉ በአቅማቸው መጠን እውቀትና ውጤት ይዘው እንዳይወጡ እያደረገ ነው። ”በተጠናቀቀው የትምህርት ዓመትም በዩኒቨርሲቲው የቆየና ሌላ ቦታ የተደረገ ክስተትን ምስል በማቀነባበር በመቱ ዩኒቨርስቲ የተደረገ አስመስሎ በተደጋጋሚ ሲሰራጭ ታዝበናል። በጣምም ስናዝንበት ነበር” ነው ያለው። ”የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ከሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች በተሻለ በመረጃና በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ እውቀት ሊኖራቸው ይገባል” ያለው ገመዳ እንደባህል ሆኖ ነገሮችን በምክንያታዊ አስተሳሰብ መተንተንና ማጣራት ሲገባን በስሜት መነዳትና ሁሉንም ነገር እውነት አድርጎ መቀበል በስፋት የሚታይ ችግር እንደሆነ መታዘቡን ነው የገለጸው። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ስለ ኮምፒዩተር አተገባበርና ስለ ኢንተርኔት አጠቃቀም ሙሉ እውቀት ስላላቸው በዚህ ውስጥ የሚሰራጩ መረጃዎችን ምንጭና አላማ ላይ የተሻለ ግንዛቤ ሊኖራቸው እንደሚገባ ነው ያመለከተው። ”በማህበራዊ ሚዲያ በሚሰራጩ ሀሰተኛ መረጃዎች ምክንያት የተነሳ እርስ በእርስ የሚጋጭ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ በአሁኑ ወቅት ማየት ያሳፍራል” ያለው ተመራቂው ተማሪዎች የአዕምሮ ብቃታቸውን በመጠቀም የመረጃዎቹን ምንነት፣ ይዘትና ምንጭ በአግባቡ መለየት እንዳለባቸው ነው ምክሩን የለገሰው። በማህበራዊ ሚዲያዎች ሀሰተኛና የጥላቻ መልዕክቶችን የሚያሰራጩ የጥፋት ዓላማ ያላቸው ግለሰቦች በዕድገት ወደፊት በመጡም ሆነ ባላደጉት ሀገራት መኖራቸውን የተናገረው ደግሞ በነርሲንግ ሙያ የተመረቀው አንዋር ታጁዲን ነው። ልዩነቱ ባደጉት ሀገራት የመረጃውን ምንነትና ምንጭ ሳያጣራ የሚጠቀም እና ለጥላቻ መልዕክቶች ጆሮ በመስጠት ጊዜውን የሚያጠፋ ዜጋ ያለመኖሩ መሆኑን ያስረዳል። "በተለይ በሀገራችን አብዛኛውን ተማሪ በፌስ ቡክ ላይ የሚሰራጩ የውሸት መልእክቶችን በማንበብ ጊዜውን ስለሚያጠፋ ተገቢ ዕውቀት ሳይገበይ ከዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ጨርሶ እንደሚወጣ ተናግሯል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች ባላደጉ ሀገራት በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የውሸት መልዕክቶች ከዕውቀት ማነስ የተነሳ እንደ እውነት ስለሚወስዱት የሀገሪቱን ሰላምና የህዝቡን በጋራ የመኖር እሴቶች እየጎዳ እንደሆነም ነው ያመለከተው። ”በሀገሪቱ ከለውጡ ወዲህ የሚዲያ ነጻነት መረጋገጡን እያስተዋልን ነው” ያለው ተመራቂ ተማሪው መንግስት በሀሰት መልዕክት ህዝብና ሀገርን ለጉዳት በሚያጋልጡት ላይ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገ ባ ነው የጠቆመው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ነገሮችን ማገናዘብ ስለሚችሉ በማህበራዊ ሚዲያ የሀሰት መልዕክቶች የተነሳ በተማሪዎች መካከል ግጭት የሚፈጠረው ለምን ባላደጉ ሀገራት ብቻ እንደሆነ ለአፍታ ቆም ብለው ሊያስቡበት እንደሚገባ መልዕክቱን አስተላልፏል። በህግ ትምህርት የተመረቀችው ፈቲያ አብዲጀባር በበኩሏ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ትምህርታቸውን ያልጨረሱ ተማሪዎች በማህበራዊ ሚዲያ የተሳሳቱ መልዕክቶች ለሚያስተላልፉ አካላት ጆሮ ካለመስጠትም ባለፈ የመረጃዎችን ምንጭ በመለየት አጥፊዎችን ማጋለጥ ይጠበቅባቸዋል። በተለይ በፌስ ቡክ የሚሰራጩ የውሸት መልዕክቶች በአንድ ጊዜ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ስዎች የሚደርስ በመሆኑ ምንጩ አንድ ሰው በመሆኑ የመረጃ ምንጮችን ለይቶ ሚዲያውን መጠቀም እንደሚገባ ነው የመከረችው። ” የማይጠቅሙ ያውም የሚጎዱ የሀሰት መልዕክቶችን በመከታተል የትምህርት ጊዜን ማጥፋት ውሎ አድሮ ጉዳቱ ለራስ ነው፣ ጸጸትም አለው ብላለች ” ። ”በአሁኑ ወቅት መንግስት የጥላቻ ንግግሮችና ሀሰተኛ መረጃዎች ረቂቅ ህግ በማዘጋጀቱ ደስተኛ ነኝ” ያለችው ተመራቂዋ መንግስት በፍጥነት ህጉን ወደ ተግባር ቢቀይር ሀገርና ህዝብን ከጉዳት መጠበቅ እንደሚቻል ተናግራለች። በማህበራዊ ሚዲያዎች ሆን ብለው የተሳሳቱ እና የጥላቻ መልዕክቶችን የሚያሰራጩ ግለሰቦች አንዱ ዓላማቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ሰላም ማሳጣት መሆኑን የተናገረው ደግሞ በማኔጅመንት እንፎርሜሽን ሲስተም የትምህርት መስክ የተመረቀው ቴዎድሮስ ፍሰህ ነው። ለዚህም ሶስት ዋና ዋና ምክንያቶችን ይጠቅሳል። የመጀመሪያው የክፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከየትኛውም ቦታ በበለጠ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ማንነቶች እና ሃይማኖቶች ያላቸው ተማሪዎች በአንድ ቦታ በመገኘታቸው ነው። ይህም በመሆኑ በቀላሉ በመካከላቸው ግጭት መቀስቀስ ይቻላል ብለው ስለሚያስቡ ነው። ሁለተኛው ደግሞ እነዚህ ግለሰቦች የጥፋት ኢላማ ያነገቡ በመሆናቸው በርካታ ተማሪዎች በአንድ ቦታ በጋራ ስለሚገኙ ግጭት ከተፈጠረ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል ከሚል እሳቤ በመነሳት መሆኑን ተናግሯል። ሦስተኛውምክንያታቸውደግሞበዩኒቨርሲቲዎችየሚገኙተማሪዎችከተለያዩአካባቢዎችየተሰባሰቡበመሆናቸውበተማሪዎች መካከልየሚፈጠረውግጭትእናየሚደርሰውጉዳት በሀገሪቱ የተለያዩአካባቢዎችበሚገኙዜጎችመካከልእርስበእርስመቃቃርእንዲፈጠርምቹ ይሆናል ብለውበማሰብነው። በመሆኑም ተማሪዎች ንቃተ ህሊናቸውን በመጠቀም በማህበራዊ ሚዲያ የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት ሀገርና ህዝቡን ለጉዳት ለማጋለጥ ከሚጥሩ ግለሰቦች ራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው ነው የመከረው። መንግስት የዜጎችን እና የሀገር ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ስላለበት በማህበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ የሀሰት የጥፋት መልዕክቶችን በራሱ አሰራር መከላከል እንዳለበት አስገንዘቧል። ኃላፊነት የጎደለው የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ባላደጉ ሀገራት በተደጋጋሚ እያስከተለ ያለውን ቀውስ በግልጽ እየተመለከትን ነው። ለምሳሌ እንኳን ከሁለት ዓመት በፊት በማይናማር በሮሂንጋ ሙስሊሞች ላይ በሀሰት በተሰራጨ የስም ማጥፋት ዘመቻ ከ700ሺህ በላይ ሰዎች ሲሰደዱ ከ 20ሺህ በላይ የሚሆኑት ለህልፈት ተዳርገዋል። በሀገሪቱ ይህ ሁሉ ጥፋት ከደረሰ በኋላ ግጭቱን ለማነሳሳት ሆን ብሎ በማህበራዊ ሚዲያ ሲለቀቅ የነበረው መረጃ የተሳሳተ መሆኑ ቢረጋገጥም አሳዛኝ ጥፋት አድርሶ አልፏል። በሀገራችንም በተለይ ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ የተረጋገጠውን የሚዲያ ነጻነት በመጠቀም በዜጎች መካከል ግጭት እንዲፈጠርና ሀገሪቱ እንዳትረጋጋ ሆን ተብሎ የሚሰራጭ የፈጠራ ወሬና የጥላቻ መልዕክት ፍጹም ከኢትዮጵያዊነት ስነ ምግባር ያፈነገጠ ነው። ተመራቂ ተማሪዎቹ እንዳሉት ሆን ብለው በማሀበራዊ ሚዲያዎች የሀሰት መረጃዎችንና የጥላቻ መልዕክቶችን የሚያሰራጩ ግለሰቦች ዋነኛ አላማቸው በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመሆኑ ተማሪዎች በዚህ ዙሪያ የጠራ ግንዛቤ ሊኖራቸው ይገባል። ራሳቸው የሀሰት መልዕክቶቹን ከመከላከል ባለፈ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ጭምር ማስተማር ይጠበቅባቸዋል። በመሆኑም በማሀበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ላይ ያለንን ባህል በመቀየርና ምክንያታዊ አስተሳሰብን ማዳበር ያስፈልጋል።በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ ያሉ ምሁራንና ተማሪዎች በተሻለ የዕውቀት ደረጃ ላይ እንደመገኘታቸው ከማንም በላይ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገንዝበው ተገቢ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። ምክንያቱም ሳይቃጠልበቅጠልነውና።