ቀጥታ፡

የቦክስ ክለቦች ውድድር በጎንደር ይካሄዳል

አዲስ አበባ ሚያዝያ 24/2010 ሶስተኛው ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር በቀጣዩ ወር በጎንደር ከተማ ይካሄዳል። ከግንቦት 15 እስከ 20 ቀን 2010 ዓ.ም በሚካሄደው ውድድር 10 ክለቦች ይሳታፉበታል ተብሎ ይጠበቃል። ውድድሩ የኢትዮጵያ የቦክስ ፌዴሬሽን በዘንድሮው ዓመት ከሚያካሂዳቸው የብሔራዊ ክለቦች የቦክስ ውድድሮች ሶስተኛው ነው። በፌዴሬሽኑ የውድድርና ስልጠና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ስንታየሁ ተስፋዬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት በውድድሩ የሚሳተፉ ክለቦች ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ ከተማ መስተዳደር እንዲሁም ከደቡብ ክልል የተውጣጡ ናቸው። ፌዴሬሽኑ ተሳታፊ ለሚሆኑ ክለቦች ውድድሩ ስለሚካሄድበት ቀን በደብዳቤ ማሳወቁን ተናግረዋል። በወንዶች ከ49 እስከ 91 ኪሎ ግራም ግጥሚያ የሚካሄድ ሲሆን፤ በሴቶች ደግሞ ከ48 እስከ 60 ኪሎ ግራም ባሉ ክብደቶች ውድድሮች ይካሄዳሉ። ውድድሩ በየክብደቱ ምርጥ ቦክሰኞችን ለብሔራዊ ቡድን በመምረጥ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ በስፖርቱ የተሻሉ ተወዳዳሪዎችን ለማፍራት እንደሚያግዝ ገልጸዋል። በተጨማሪም ለቦክስ ክለቦች የውድድር አማራጮችን ማስፋትና አቅማቸውን እንዲፈትሹ የውድድሩ መካሄድ ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቅሰዋል። የመጀመሪያና የሁለተኛ ዙር ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድሮች በአዲስ አበባና በሆሳዕና ከተማ መካሄዱን አስታውሰው የመጨረሻው የክለቦቹ ውድድር ሰኔ አጋማሽ 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ጠቁመዋል። በኢትዮጵያ ከ1950ዎቹ ጀምሮ የቦክስ ስፖርት እንደ አንድ የስልጠና ዓይነት ለወታደሮች ይሰጥ ነበር። በተለይ በሐረር ጦር አካዳሚ የሚያሰለጥኑት እንግሊዞች በመሆናቸው የቦክስ ስፖርትን እንደ ዋነኛ የስልጠና ዓይነት ይሰጡ ነበር። የክለቦች ምስረታም በዛው ወቅት የተጀመረ ሲሆን፤ በሰራዊቱ ውስጥ ከተቋቋሙ ክለቦች መካከልም የክቡር ዘበኛ፣ መኩሪያ፣ ምድር ጦር፣ ፖሊስ፣ ፈጥኖ ደራሽ የሚባሉ ክለቦች ይጠቀሳሉ።
5270
 
1589
 
945
 
213
 
8946
 
813
 
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም