ሲቪክ ማህበራት ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ የሚጠበቅባቸውን ሚና አልተወጡም - ኢዜአ አማርኛ
ሲቪክ ማህበራት ለሕግ የበላይነት መረጋገጥ የሚጠበቅባቸውን ሚና አልተወጡም
ሐምሌ 2/2011 በአገሪቱ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ሲቪክ ማህበራት ከፍተኛ ሚና ቢኖራቸውም አብዛኞቹ የሚጠበቅባቸውን አለማበርከታቸው የተለያዩ ሲቪክ ማህበራት ጠቆሙ። ኢዜአ ካነጋገራቸው ማህበራት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ መሰረት አታላይ እንደተናገሩት የህግ የበላይነትን ማስከበር የመንግስት ዋና ስራ ቢሆንም ሲቪክ ማህበራትም ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ጋዜጠኞች ህብረተሰቡ ለህግ መከበር የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ፤ እንዲያስተምሩ ና እንዲያሳውቁ ማህበሩ ትልቅ ኃላፊነት አለበት ነው ያሉት። በአሁኑ ወቅት አንዳንድ ሚዲያዎች የሕግ የበላይነት እንዲጣስ፣ አገሪቷ ሰላም እንዳትሆን እንዲሁም ብሄር ከብሄር እንዲጋጭ የሚሰሩትን ስራ ማህበሩ እንደሚያወግዝም አስታውቋል፡፡ ማህበሩ የሕግ የበላይነት እንዲከበር ከሚዲያዎችና ከሌሎች አካላት ጋር የሰራው ስራ በቂ አይደለም ያሉት አቶ መሰረት፤ በሕግ የበላይነት፣ በዲሞክራሲ ግንባታና በሌሎች ወሳኝ ጉዳዮች ላይ በትኩረት ለመስራት ዝግጁ መሆኑንም ገልጸዋል። የሕግ የበላይነት ካልተከበረ ሀገር እንደ ሀገር የማትቀጥል መሆኑን የተናገሩት የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ደበበ ገብረጻድቅ ፤ ለህግ የበላይነት መከበር ጥረት ማድረግ ያለበት መንግስት ብቻ ሳይሆን የመላውን ዜጋ ተሳትፎ ያስፈልጋል ብለዋል። የሲቪክ ማህበራት እየሰሩ ያለው ስራ በቂ ባለመሆኑም ቀጣይ በሕግ የበላይነት ላይ ለህብረተሰቡ ግንዛቤና ትምህርት መስጠት እንደሚጠበቅባቸውም ጠቅሰዋል። ማህበራቱ በህግ የበላይነት ላይ ከሚሰሩ የመንግስት ተቋማት ጋር በቅርበትና በቅንጅት በመስራት ህብረተሰቡ ያለውን ግንዛቤ በማዳበርና አስፈላጊውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ማገዝ ይቻላል ብለዋል። “የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር የተለያዩ ጥያቄዎች ቢኖራቸውም፤ ጥያቄዎቹን በማቆየት በከተማዋ የብሄራዊ ፈተናዎች በሰላማዊ ሁኔታ እንዲጠናቀቁ የሚጠበቅበትን ሚና መጫወቱን ገልጸዋል። ማህበሩ በቀጣይም በአገሪቷ ሰላም እንዲሰፍንና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ከትምህርት ማህበረሰብ ጋር ብቻ ሳይሆን ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያ ብሄራዊ ዓይነስውራን ማህበር የህዝብ ግኑኝነት የቅርንጫፎችና የአባላት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ገብሬ ተሾመ በበኩላቸው፤ የሕግ የበላይነት ጥሰቱ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ በዚህ ችግር ዓይነ ስውራን ተጎጂ እየሆኑ ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የነበሩት አፋኝ ህጎችና መማሪያዎች፤ የሲቪክ ማህበራት የሕግ የበላይነት እና ሎሎች ጉዳዮች ላይ እንዳይሰሩ እንቅፋት ሆኖ ነበር ያሉት አቶ ገበሬ፤ አሁን የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በአገሪቱ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የነበሩት አፋኝ ህጎችና መማሪያዎች፤ የሲቪክ ማህበራት የሕግ የበላይነት እና ሎሎች ጉዳዮች ላይ እንዳይሰሩ እንቅፋት ሆኖ ነበር ያሉት አቶ ገበሬ፤ አሁን የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በአገሪቱ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።