ቀጥታ፡

በስሜት ላይ ከተመሰረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ይልቅ ለሀገር መረጋጋት እንሰራለን -  ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች

ሐምሌ 1/2011 (ኢዜአ) አሁን በገሪቱ  እየተስተዋለ ካለው በስሜት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ  እንቅስቃሴን በመፍታት ለሀገር ሰላምና መረጋጋት እንደሚሰሩ  አስተያየታቸውን የሰጡ ተፎካከሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች  ተናገሩ። የህግ የበላይነት እንዲከበር ና ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ፤ ስልጣን በህዝብ ድምጽ ብቻ እንዲመጣና  ህዝቡ በጽናት እንዲታገል፤ ደጋፊና አባሎቻቸውን እያስተማሩ እንደሆነ የኦሮሚያ ብሄራዊ ፓርቲ የአደረጃጀትና ፖለቲካ ጉዳይ ኃላፊ አቶ ተማም ባቲ ገልጸዋል። “የህግ የበላይነት መከበርና የህዝብ ነጻነት መጠበቅ የማይነጣጠሉ ናቸው” ያሉት ሃላፊው ህግ የሚተላለፉትን ለይቶ ለህግ ለማቅረብ  ህዝቡ ተገቢው መረጃ ኖሮት እንዲተባበር ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል። የፓርቲዎች ውስጠ ዴሞክራሲ መኖር ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ መሰረት በመሆኑ ችግሮችን በመደማመጥ መፍታት መቻል ህዝብን የመምራት አቅም ማሳያ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ልዩነትን አክብሮ አማራጭ ሀሳብ ለህብረተሰቡ በማቅረብ ሀገርን መገንባት  የግድ ነው ሲሉ “አሁን የተከሰተው ችግር የዚህ እጦት ነው “ብለውታል፡፡ ሰሞኑን ስልጣንን በሃይል ለመያዝ የተከሰተው ችግር ዘመኑን የማይመጥንና አሳዛኝ  ተግባር ነው ያሉት አቶ ተማም፤ ኢህአዴግ ውስጠ የዴሞክራሲውን  መፈተሽ እንዳለበት ና ህዝቡም ለውጡ እንዳይቀለበስ የበኩሉን ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች የሃሳብ ልዩነትን ያለማክበር ችግርን፤ አስተሳሰብን እና  የራስን ሀሳብ ለመጫን የሚደረግ ጥረትን በጋራ መፍታት ይገባልም ብለዋል። “ሁሉም ፓርቲ የተደራጀው ህገ-መንግስቱን አከብራለሁ ብሎ ነው፤ ህገ መንግስቱ ደግሞ ጉድለት የለውም ብሎ መናገር ያስቸግራል”  ያሉት ሃላፊው፤ ያለውን ጉድለት በውይይት ማረም መፍትሔ መሆኑን ጠቁመዋል። በህግ ማስከበር ሂደት ለዜጎች መብት መከበር ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ገልጸው፤ የዴሞክራሲ ባህል እንዲዳብር በመስራት “ለህዝቡ አማራጭ መሆናችንን እናስመሰክራለን” ነው ያሉት፡፡ የኢትዮጵያ ማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ  በበኩላቸው፤ ሀገሪቱ  በለውጥ  ጅማሮ ላይ  በነበረችበትና  ህዝቡ ልዩነቶቹን በዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚንፈታበት ግዜ ይመጣል ብሎ በጠበቀበት፤ ጉዞውን የሚያደናቅፉ ችግሮች  መከሰታቸው የህብረተሰቡን ተስፋ ለማጨለም ያለመ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ በፊት የነበረ የመታሰር፣ የመሳደድና መገዳደል ፖለቲካ ለሀገር ጠቃሚ የሆኑ ሰዎችን ከፖለቲካው  ማራቁን ና ልዩነትን በሀይል ለመፍታት  እንዲሞክሩ ያደረገ  በመሆኑ  ህዝቡ ካለፈው ችግር መማር እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡ ፓርቲያቸው ለሰላማዊና ህጋዊ ፖለቲካ ሽግግር አባላቱና ደጋፊዎቹ የበኩላቸውን እንዲያበረክቱ ግንዛቤ መሰጠቱን የገለጹት የህዝብ ግንኙነቱ፤ በስሜት ላይ ከተመሰረተ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ይልቅ ለሀገር መረጋጋት እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡ በስራ ላይ ያለውን ህገ-መንግስት በማክበር ለህዝቡ አማራጭ ሀሳብ  የሚያቀርቡበትን እድል ለመፍጠር በህጋዊና በሰላማዊ  መንገድ እንደሚሰሩም አስረድተዋል፡፡ “የህግ የበላይነት  መከበር ለሁላችንም ዋስተና ነው” ያሉት አቶ ናትናኤል ለተግባራዊነቱ  በወንጀል የሚጠረጠሩ ሰዎች ሰብአዊና ዴሞክራሲያ መብቶታቸው መከበር እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል ፡፡ ህዝቡም ለወንጀል መከላከል ስራ ከመንግስትጋር  መተባበርና  ለጥያቄዎቹ  ምላሽ በትእግስት መጠበቅ እንዳለበትም ገልጸው፤ የተጀመረውን ለውጥ ከዳር ለማድረስ  እርምጃ ከመውሰድ ጎን ለጎን ችግሮቹን አስቀድሞ መከላከል ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ነው ያሉት።                
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም