በፈረቃ ኤሌክትሪክ መጠቀም በመኖሪያ ቤቶች ላይ ከዛሬ ጀምሮ እንዲቀር ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በፈረቃ ኤሌክትሪክ መጠቀም በመኖሪያ ቤቶች ላይ ከዛሬ ጀምሮ እንዲቀር ተደረገ
ሐምሌ 1/2011 ላለፉት ሶስት ወራት ሲተገበር የነበረው የኤሌክትሪክ ፈረቃ አገልግሎት በመኖሪያ ቤቶች ላይ ከዛሬ ጀምሮ እንዲቀር መደረጉን የውሃ፣ መስኖና እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ። ለአነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ተጠቃሚዎች ግን ብዙ ተጠቃሚ ባለበት ሰዓት 50 በመቶ አቅማቸው እንዲሁም ከምሽቱ 5 እስከ ንጋት 12 ሰዓት በሙሉ አቅማቸው መጠቀም ይችላሉ ተብሏል። የውሃ፣መስኖናና ኢነርጂ ሚንስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከዛሬ ጀምሮ የኤሌክትሪክ ፈረቃ አጠቃቀም በመኖሪያ ቤቶች ላይ ተግባራዊ አይሆንም። ሆኖም በሚቀጥሉት 15 ቀናት ለአነስተኛ፣ መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ተጠቃሚዎች ብዙ ተጠቃሚ ባለባቸው ሰዓታት 50 በመቶ አቅማቸው ብቻ እንዲሰሩ ይገደዳሉ። ብዙ ተጠቃሚ ከሚስተናገድባቸው ሰዓታት (ፒክ አወር) ውጭ ከምሽቱ 5 ሰዓት እስከ 12 ሰዓት ግን ኢንዱስትሪዎቹ በሙሉ አቅማቸው መጠቀም እንደሚችሉ ተናግረዋል። በሚቀጥሉት 15 ቀናት ውሰጥ ያለውን ሁኔታ በማየት በቀጣይ ማሻሻያዎች ሊደረጉ እንደሚችሉም ሚኒስትሩ ገልፀዋል። እንደ አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚዎች የሚያገኙትን ሃይል በቁጠባ እንዲጠቀሙም ጥሪያቸውን አቅርቧል። የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከግንቦት 1 እስከ ሰኔ 30 ቀን 2011 ዓ.ም በፈረቃ ሲሰጥ መቆየቱ ይታወቃል። እንደ ሚኒስትሩ ገለፃ የገናሌ ዳዋ ግድብ 3 የኤሌክትሪክ ማመንጫ የፊታችን ነሃሴ ወር አጋማሽ ላይ 250 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ይጀምራል። የአይሻ የጸሃይ ኃይል ማመንጫም በቀጣዩ አመት አጋማሽ እስከ 125 ሜጋ ዋት ማንጨት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል። በመሆኑም እዚህና ሌሎች አማራጮችን በማስፋት በአገሪቷ እያጋጠመ ያለውን የሃይል እጥረትና አቅርቦት ለማሻሻል ጥረት ይደረጋል ተብሏል።