የክልሉን ከፍተኛ አመራሮች የመተካት ስራ እየተሰራ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉን ከፍተኛ አመራሮች የመተካት ስራ እየተሰራ ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ
አዲስ አበባ ሃምሌ 1/2011 በአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላትና አመራሮችን ለመተካት በጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ። አዴፓ ህይወታቸውን ያጡ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችን ዓላማ የሚያስቀጥሉ ተተኪ አመራሮች እንዳሉትም አመልክተዋል። ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በክልሉ በተሞከረ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ርዕሰ መስተዳድሩን ዶክተር አምባቸው መኮንን ጨምሮ ሶስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ህይወታቸውን ማጣታቸው ይታወሳል። በመፈንቅለ መንግስት ሙከራው አቀነባባሪነት የተጠረጠሩት የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ሃላፊ ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው ጽጌ ሲሸሹ በጸጥታ ሃይሎች እንደተገደሉ መገለጹ ይታወቃል። በዚህም በክልሉ የአመራር ክፍተት በመፈጠሩ ይህንን ክፍተት ለመሙላት እየተሰራ እንደሆነ አቶ ደመቀ ገልጸዋል። የአመራር ክፍተቱን ለመሙላትም አዴፓ በከፍተኛ ጥንቃቄ ተተኪ አመራሮችን ለመምረጥ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አቶ ደመቀ ገልጸዋል። አዴፓ አቅሙን ለማሳደግ ወጣት ምሁራንን ወደ ፊት በማምጣት የጀመረው ስራ መኖሩን ጠቅሰው ባልታሰበ ሁኔታ በአመራሮቹ ላይ በደረሰው ጉዳት ያጋጠመውን ጉድለት ለመሙላት እየተሰራ ነው ብለዋል። ''ካጋጠመን ጸጸት የምንወጣው ዓላማቸውን ወደ ከፍታ በማድረስ ነው'' ያሉት አቶ ደመቀ በየደረጃው ያለው ህዝብ ክልላዊና አገራዊ የለውጥ ንቅናቄውን ውጤታማ ለማድረግ እንዲረባረብ ጠይቀዋል። ከድርጊቱ በኋላ በአሁን ጊዜ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ በተሻለ ሁኔታ ላይ እንደሆነም ነው አቶ ደመቀ የገለጹት። ለዚህ ደግሞ የጸጥታ አመራሩ ላይ የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት የተሰራው ስራ ቅድሚያ የተሰጠው መሆኑን አንስተዋል። በክልሉና በአገር ደረጃ ያጋጠመው ጥቃት አገራዊ ለውጡን የሚፈታተን ቢሆንም የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ ልብ የደገፈው ለውጥ በመሆኑ ስኬቶቹን እያጠናከሩ ተግዳሮቶቹን በጋራ ለመፍታት መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል።