ቀጥታ፡

የወንጀል ድርጊት ፈጻሚዎችን ወደህግ የማቅረቡ ሂደት ከበቀልና ከመጠቃቃት የፀዳ ሊሆን ይገባል ተባለ

ሐምሌ 1/2011 የወንጀል ድርጊት ፈጻሚዎችን ወደህግ የማቅረቡ ሂደት ከበቀልና ከመጠቃቃት የፀዳ እንዲሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አሳሰቡ። ተጠርጣሪዎችን ወደህግ የማቅረቡ ስራ ህግን የተከተለና ፌዴራላዊ ስርዓቱን ያከበረ መሆን እንዳለበትም ነው አቶ ደመቀ የገለጹት። የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ሊቀመንበር ጭምር የሆኑት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአማራ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክቶ ዛሬ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል። በዚሁ ጊዜ ሰሞኑን በክልሉና በፌዴራል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በክልልና በፌዴራል ደረጃ የወንጀሉ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ የሚደረጉ ጥረቶች በጥንቃቄ መካሄድ እንዳለባቸው አሳስበዋል። ለጥርጣሬ የሚያበቁ ጭብጦችን በአስተውሎት መመልከትና አንድ ተጠርጣሪ በህግ ጥላ ስር እንዲውል ሲደረግ የሚመለከተው አካል እያወቀ መሆን እንዳለበትም አስገንዝበዋል። የወንጀል ድርጊቱ ፈጻሚዎችን የመለየት ስራ በጥበብ፣ በህግና ስርዓት ብቻ በአግባቡ ሊፈጸም እንደሚገባ ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት። ለዚህ ደግሞ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በከፍተኛ ጥንቃቄ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል። በአገራዊ ለውጡ አካሄድ ላይ ቅሬታ ያለውም ሆነ ሌሎች ጥያቄዎችን በማንሳት የተለየ ሀሳብ ይዘው የሚታገሉ ዜጎችን ወደ ወንጀል ድርጊቱ ከማጠጋጋት መቆጠብ እንደሚገባም  ነው  ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያብራሩት። በሌላ በኩል የሌላ ፓርቲ አባልም ይሁን ሌላ አካል በድርጊቱ የተሳተፈ ከሆነ በዚህ ላይ መደራደር አይገባም፤ ህግ መከበር አለበት ብለዋል። ከሁለት ሳምንታት በፊት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የነበሩትን ዶክተር አምባቸው መኮንንን ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በደረሰባቸው ጥቃት ህይወታቸው አልፏል። የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊች ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ በተወሰደው እርምጃ እስከ ትናንት ድረስ በባህርዳር 213 በመፍንቅለ መንግስቱ በመሳተፍ የተጠረጠሩ በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፡፡ በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥም የክልሉ ልዩ ሃይል አመራር አባላት፣ የክልሉን የጸጥታ መዋቅር የሚመሩ ከፍተኛ ሃላፊዎች እና አባላት እንዲሁም ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች እንደሚገኙበት ትናንት ምሽት የፀጥታና ፍትህ የጋራ ግብረ ኃይል በሰጠው መግለጫ አመልክቷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም