ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊያን ሃጃጆች ከፊታችን አርብ ጀምሮ ወደ ሳኡዲ ጉዞ ይጀመራሉ

አዲስ አበባ ሃምሌ 1/2011ለዘንድሮው የሃጅ ስነ- ስርአት ኢትዮጵያዊያን ሃጃጆች ከፊታችን አርብ ጀምሮ ወደ ስፍራው እንደሚጓዙ ተገለጸ። የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የዘንድሮውን የሃጅ ጉዞ አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ተጠባባቂ ዋና የንግድ ጉዳዮች ኦፊሰር አቶ ኢሳያስ ወልደማርያም በዚሁ ወቅት እንደገለጹት አየር መንገዱ የዘንድሮ የሀጅ ተጓዦችን ከሐምሌ 5 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ማጓጓዝ ይጀምራል። በመጀመሪያው ቀን በረራ በአየር መንገዱ 268 ተጓዦች ወደ ስፍራው የሚያቀኑ ሲሆን እስከ ሐምሌ 23 ቀን 2011 ዓ.ም ተጓዦችን ወደ ስፍራው ያደርሳል ብለዋል። አየር መንገዱ ደርሶ መልስ አጠቃላይ 38 በረራዎችን ያዘጋጀ መሆኑንና በአጠቃላይ አሁን ባለው ሄኔታ 5 ሺህ ተጓዦች የበረራ አገልግሎት እንደሚሰጥና ሌሎች 5 ሺህ ተጓዦች በሳዑዲ አየር መንገድ አገልግሎት እንደሚያገኙም ታውቋል። የሃጅ ጉዞን አስመልክቶ ከአየር መንገዱና ከእስልምና ጉዳዮች ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን ለተጓዦች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እየሰራ መሆኑም ተገልጿል። በሳዑዲ አረቢያ ለተጓዦች አገልግሎት የሚያግዙ ከ30 በላይ የአየር መንገዱ ሰራተኞች ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ኢሳያስ በመካ፣በመዲና እና ጅዳ ከሳዑዲ አየር መንገድ ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል። ከነሐሴ 14 እስከ ጳጉሜን 2 ቀን 2011 ዓ.ም ደግሞ የሃጅ ስነ ስርአታቸውን ፈፅመው ወደ አገራቸው የሚመለሱ ይሆናል። በዘንድሮው የሃጅ ጉዞ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ከ40 ሺህ በላይ ደንበኞችን ለማስተናገድ ከ228 በላይ በረራዎችን ለማድረግ ተዘጋጅቷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም አየር መንገዱ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ጋር በመሆን የዘንድሮው የሀጅ ጉዞ ውጤታማ እንዲሆን አስፈላጊውን ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል። በቪዛ አሰጣጥ፣ የመረጃ ልውውጥና ምዝገባ ዙሪያ በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። የሃጅ ተጓዦች ቁጥር አሁን ካለው መጠን ቢጨምርም አየር መንገዱ ተጨማሪ አውሮፕላኖችን በማዘጋጀት አገልግሎት ይሰጣል ብለዋል። በሳዑዲ አረቢያ ወቅቱ ሞቃት በመሆኑና የበርካታ አገራት ተጓዦች በመኖራቸው መጨናነቅ ሊፈጠር እንደሚችል በማሰብ ችግሮችን ለመፍታት አየር መንገዱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር  እንደሚሰራም አረጋግጠዋል። በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የሃጅና ኡምራ አስተባባሪ ሸህ አንዋር ሙስጠፋ እንዳሉት በዘንድሮው የሃጅ ጉዞ የሳኡዲ መንግስት እስካሁን ለ10 ሺህ ኢትዮጵያዊያን ፈቅዷል። የተጓዦች ፍላጎት በመጨመሩ ለ5 ሺህ ተጨማሪ ተጓዦች ፈቃድ እንዲሰጠው በምክር ቤቱ በኩል ለሳኡዲ የሃጂ ሚኒስቴር ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ በመጠባበቅ ላይ መሆኑንም ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የኡለማዎች ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ኡመር እድሪስ ኢትዮጵያ በሳውዲ ሃጅ ሚኒስቴር ለሀጅ ጉዞ 43 ሺህ 337 ሰዎች ኮታ ቢኖራትም በተለያዩ መክንያቶች ልትጠቀምበት እንዳልቻለች ገልጸዋል። በምክር ቤቱ ቀድሞ ያለመመዝገብና አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አለማድረግ እንዲሁም በተጓዦች በኩል ባሉ ችግሮች ምክንያት ኮታውን በአግባቡ መጠቀም ያልተቻለባቸው ምክንያቶች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል። በቀጣዩ ዓመት የሃጂ ጉዞ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ኮታውን በአግባቡ ለመጠቀም ይሰራልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም