ቀጥታ፡

ለፌዴሬሽኑ ማደግ ጉልህ አስተዋጽኦ ላደረጉ አንድ ሰራተኛ የ30 ግራም ወርቅና የ200 ሺህ ብር ሽልማት ተበረከተ

ሐምሌ 1/2011 የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እንዲጠናከር ጉልህ ሚና ተጫውተዋል ላላቸውና ዘንድሮ በጡረታ ለተሰናበቱ አንድ ሰራተኛው የ30 ግራም ወርቅና የ200 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት አበረከተ፤ በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴነት ላገለገሉ አትሌቶችም የወርቅ ሽልማት ተበርክቷል። የወርቅና ገንዘብ ሽልማቱ  የተበረከተላቸው ሸዋነሽ ገዛህኝ በፌዴሬሽኑ ግዥና ፋይናንስ፣ የጽህፍት ቤት ኃላፊ ተወካይና በሌሎች የተለያዩ የሥራ ዘርፎች ላለፉት 13 ዓመታት አገልግለዋል። ወይዘሮ ሸዋነሽ ፌዴሬሽኑ ከመንግስት የበጀት ድጎማ ተላቆ በገንዘብ አቅሙ እራሱን እንዲችል ለማድረግና ኃብት እንዲያፈራ ትልቅ ሚና በመጫወት የፌዴሬሽኑን አጠቃላይ እንቅስቃሴ እንዲጠናከር ቁልፍ ሚና መጫወታቸው በሽልማት ስነ-ስርዓቱ ላይ ተመልክቷል። ከእነዚህ ስራዎች መካከል ከስፖርት ትጥቅ አምራቹ አዲዳስ ኩባንያ ጋር በመነጋገር ፌዴሬሽኑ ገንዘብና የስፖርት ትጥቅ እንዲያገኝ አድርገዋል። እንዲሁም ፌዴሬሽኑ  በአዲስ አበባ ከተማ ጉድር ሾላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የራሱን ባለሶስት ፎቅ ህንጻ ገንብቶ የህንጻ ባለቤት እንዲሆንም ቁልፍ ሚና መጫወታቸውም ተገልፇል። ከዚህም ሌላ ፌዴሬሽኑ በ17 ሚሊዮን ብር ወጪ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ አካባቢ ባለ 8 ፎቅ ህንጻ እንዲገዛ የበኩላቸውን ሚና ተወጥዋል። ፌዴሬሽኑ በእነዚህ ህንፃዎች አማካኝነትም በአሁኑ ወቅት በየወሩ እስከ ሰባት ሚሊዮን ብር የሚደርስ ገቢ ባለቤት መሆን ችሏል ነው የተባለው። ፌዴሬሽኑ እነዚህ ስራዎችን ከሙያ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን የአንበሳውን ድርሻ ለተወጡት ለወይዘሮ ሸዋነሽ ገዛህኝ ነው ሽልማትና እውቅና የሰጠው። ከእሳቸው በተጨማሪ አትሌቶችን ወክለው በፌዴሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ አባልነት ላገለገሉት ለአትሌት መሰረት ደፋርና ለአትሌት ስለሺ ስህን 20 ግራም ወቅር ሽልማት ከፌዴሬሽኑ ተበርክቶላቸዋል። ከፌደሬሽኑ በተጨማሪ የኢትዮጵያ አትሌቶች ማህበር ባለፉት አራት ዓመታት ማህበሩን ላገለገሉና በአዲስ አመራር ለተተኩት ለአትሌት የማነህ ጸጋዬ፣ ሞስነት ገረመው፣ ፋንቱ ማጌሶ ፣አትሌት ስለሺ ስህንና መሰረት ደፋር የጣት የወርቅ ሸልማት አበርክቷል። ከሽልማቱ በኋላ ወይዘሮ ሸዋነሽ ባደረጉት ንግግር በፌዴሬሽኑ ባደረጉት ቆይታ ስራቸውን ወደውት ይሰሩ እንደነበርና ከሌሎች  የስራ ባለደረቦቻቸውም ጋር በመተባበረ ስኬታማ ስራ ማከናወናቸውን ተናግረዋል። ፌዴሬሽኑ እውቅና በመስጠቱ ምስጋናቸውን አቅርበው  በቀጣይም ፌዴሬሽኑ በማናኝውም መልኩ የእሳቸውን እገዛ ከፈለገ በነጻ ለማገልገል ቃል ገብተዋል። የአትሌቶች ማህበርን ባለፉት አራት ዓመታት ያገለገሉትና ከማህበሩና ከፌዴሬሽኑ ሽልማት የተሰጣቸው አትሌቶችም  በቀጣይም በማንኛውም ጊዜ ከአትሌቲክሱ ጎን በመቆም ለስፖርት  እድገት እንደሚሰሩ ነው የተናገሩት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም