ቀጥታ፡

መንግስት የተጠያቂነትን መርህ አንግቦ ለህግ የበላይነት መረጋገጥ በቁርጠኝነት መስራት አለበት ….የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሙሁራን

ሐምሌ 1/2011 በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥና የህግ የበላይነት እንዲከበር ህግን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ማድረግና አጥፊዎችን በህግ ተጠያቂ ማድረግ መሠረታዊ ጉዳዮች መሆናቸውን የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሙሁራን ተናገሩ። ሙሁራኑ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንደተናገሩት የሀገራዊ ለውጥ አመራሮች መስለው ለውጡን የሚያደናቅፉ አካላትን በየጊዜው ፈትሾ እርምጃ በመውሰድ ለሁሉም የምትበጅ ሀገር የመገንባቱን ጅምር ከዳር ማድረስ ይገባል፡፡ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል መምህር አቤል ልዑልሰገድ የህግ አውጪው፣ የህግ አስፈጻሚውና የህግ ተርጓሚው አካላት በህገ-መንግስቱ የተቀመጡ መብቶችና ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች እንዲከበሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተቀናጅተው መስራት አለባቸው፡፡ መንግስት ለዜጎች ህግና ግዴታቸውን እያሳወቀ ካልሄደ አሁን እየተስተዋለ እንዳለው ሰዎች ፍትህን በራሳቸው የማግኘት ሂደት ውስጥ እንደሚገቡ አመልክተዋል። ህግን ተደራሽ ማድረግና በየጊዜው ማስተማር በሀሳብ ልዕልና የመገዛትንና በውይይት የማመንን ባህል እየጎለበተ እንዲመጣ እንደሚያግዝም ነው መምህሩ የገለፁት፡፡ በአሜሪካ ሀገር ከህጻንነት ጀምሮ በእያንዳንዱ ዕድሜ እርከን መሠረታዊ ህጎች በሁሉም ትምህርቶች ተካቶ መሰጠቱ ለሀሳብ ልዕልናና በውይይት የሚያምን ትውልድ ለመፍጠር ማገዙን በአብነት ጠቁመዋል፡፡ አቶ አቤል እንዳሉት በኢትዮጵያም መንግስትና በህግ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ወደ ህብረተሰቡ በመውረድ ህግና ግዴታን ማስተማር አለባቸው። “ይህ ከሆነ በውይይት ለመግባባት፣ ወደ ዘላቂ ለውጥና ሰላም ለመጓዝ መደላደል ይፈጥራል” ብለዋል፡፡ በማህበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶችና ብዙሃን መገናኛዎች ሰውን ወደ ስሜታዊነት በማስገባት እሳት በመለኮስ ሰላም ከማደፍረስ ይልቅ በሀገር ጉዳይ ላይ የውይይት ባህል እንዲዳብር ትኩረት ቢሰሩ የተሻለ ውጤት እንደሚመጣም አቶ አቤል መክረዋል። በውይይትና በመነጋገር ብሎም ለተሻለው ሃሳብ ያለመገዛትንና ያለማመንን ጉዳይ የሚያስከትለውን ችግር ከጎረቤት ሩዋንዳ መማር እንደሚገባ ነው መምህር አቤል ያሳሰቡት፡፡ በዩኒቨርሲቲው ሌላው የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ተመስገን ደሳለኝ በበኩላቸው እንዳሉት ሰዎች በቡድን እንዳሻቸው እየተንቀሳቀሱ፣ ክልሎችም ልዩ ኃይል በሚል ኢህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ ጦር እያደራጁ በዝምታ መታለፉ ሀገሪቷን ዘመናት ያሻገሩ ህጎች እንዲጣሱ በር ከፍቷል፡፡ “ይህም የሀሳብ የበላይነትና የህግ ልዕልና ቦታ እንዳይሰጠው ምክንያት እየሆነ ነው” ብለዋል፡፡ ሰሞኑን በሀገራችን የተፈፀመውና የተከሰተው ክስተት የህግ የበላይነት በሚፈለገው ልክ ላለመረጋገጡ ማሳያና መማሪያ ሊሆን እንደሚገባም አቶ ተመስገን ተናግረዋል፡፡ እንደ ባለሙያው ገለጻ የፌደራል መንግስት ለሀገር ሰላምና መረጋጋት የጎላ ጠቀሜታ ያለውን የተጠያቂነት አሰራር ለማስፈን በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል። በቅርቡ የፌደራል መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ቁርጠኝነቱን ማሳየቱ የሚበረታታ መሆኑንም ነው የጠቆሙት። ተመሳሳይ ሀሳቦችን የተጋሩት በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል ኃላፊ አቶ አሰፋ ካሳ “የህግ የበላይነትና የተጠያቂነት መንፈስ መጥፋት ለውጡ በሁለት እግሩ እንዳይቆምና ሀገሪቷ እንዳትረጋጋ አድርጓታል ብለዋል፡፡ የጠበበ ቀበሌያዊ አስተሳሰብ እንደ ብሔር፣ እንደ ቡዱን የኔ ብቻ የማለት አዝማሚያ ለእዚች ሀገር መፃኢ ጉዞ እንደማይበጅም አስገንዝበዋል፡፡ እንደ ሙሁሩ ገለጻ ቡዱኖች በጉልበት ህግን ጥሰውና የሀሳብ የበላይነትን ደፍጥጠው ጥቅማቸውን የሚያስከብሩት በሁለት መሠረታዊ ምክንያት ነው፡፡ “አንድም ጠበቅ ያለ የህግ የበላይነትና ተጠያቂነት ያለመኖር ሲሆን፤ በሌላ በኩል የሰለጠነና የተሻለ ሃሳብ ይዞ ከማሸነፍ ይልቅ ለራስ ጥቅም ሲባል የሚከወን ተግባር ነው” ብለዋል፡፡ በቅርቡ በባህር ዳር ከተማና በአዲስ አበባ የተፈፀመው ክስተት የእዚህ ዋና ማሳያና እንደማንቂያ ደውል ሊወሰድ እንደሚገባም አቶ አሰፋ አመልክተዋል፡፡ “ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት ይዞት የመጣውን በሀሳብ የበላይነት የማመንና የመግዛት ፍልስፍና ህዝቡ እንዲቀበል ለማድረግ ጊዜ ስለሚጠይቅ መንግስትም ያለመሰልቸት ማስተማር ይኖርበታል” ብለዋል፡፡ ‹‹ የጡንቻ አስተሳሰብ ለማንም አይጠቅምም፤ የህብረተሰቡም የፖለቲካ ንቃት እየጨመረ በመምጣቱ በጉልበት የሚገዛ ዜጋ ከእዚህ በኋላ አይኖርም “ ብለዋል ሙሁሩ። በመሆኑም መንግስት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮች የህግ የበላይነትን በማመን ስራቸውን ማከናወን እንዳለባቸው ነው የገለጹት። በተለይ መንግሥት የህግ ተጠያቂነትን ከማስፈን አንጻር ብዙ ሊሰራ እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት፡፡ እንደ ሙሁራኑ ገለጻ ሀገሪቱ የሁሉም በመሆኗ የሃሳብ ልዩነትንና ብዝሀነትን በማክበር የተሻለች ሀገር ለመገንባት ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል። ይህን ለማድረግ ከትላንት ችግሮች በመማር በሰከነ መንፈስ ለዛሬ መደላድል መፍጠር እንደሚገባ ነው ያስታወቁት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም