የኢትዮጵያ የ2012 ዓ.ም በጀት ፀደቀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የ2012 ዓ.ም በጀት ፀደቀ

ሀምሌ 1/2011 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የ2012 በጀት የፌዴራል መንግስት በጀት 386 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ሆኖ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ፀደቀ:: ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ በ2012 በጀት ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት በዝርዝር ተወያይቷል። በመጨረሻም የ2012 የፌዴራል መንግስት በጀት 386 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር እንዲሆን በምክር ቤቱ በሙሉ ድምጽ ፀደቋል። የጸደቀው በጀት ከ2011 በጀት ጋር ሲነጻጻር የ 6 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ጭማሪ አለው። በዚህም መሰረት ለመደበኛ ወጪዎች 109 ነጥብ 46 ቢሊዮን ብር፣ ለካፒታል ወጪዎች 130 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር፣ ለክልል መንግስታት የሚሰጥ ድጋፍ 140 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብርና ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 6 ቢሊዮን ብር ተመድቧል። በጀቱ ባለፈው ዓመት ቅድሚያ ከተሰጣቸው የሰው ኃይልና የመሰረተ ልማት ግንባታ በተጨማሪ በምግብ ዋስትና ራስን ለማስቻል፣ ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም ለመስኖ ልማትና ግድብ ስራዎች ትኩረት ሰጥቷል። መንግስት ከአገር ውስጥ የገቢ ምንጮችና ከውጭ እርዳታ 289 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዷል። የዓመቱ በጀት የ97 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ጉድለት እንዳለበት ተመልክቷል። የበጀት ጉድለቱን በቀጥታ በጀት ድጋፍና በፕሮጀክቶች ከሚገኝ 40 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብድር እና ከሀገር ውስጥ ከሚገኝ 56 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ብድር ለመሸፈን ታቅዷል። የተጠናቀቀው በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት በጀት 346 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ነበር።