በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዳግም መሪነቱን ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ተረክቧል - ኢዜአ አማርኛ
በእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዳግም መሪነቱን ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ተረክቧል
ሰኔ30/2011 /ኢዜአ/ በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዳግም መሪነቱን ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ተረክቧል። በፕሪሚየር ሊጉ ዛሬ ረፋድ ባህዳር ላይ በተካሄደ የ19ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጎንደር ከተማን 34 ለ 30 በሆነ ውጤት አሸንፏል። ውጤቱንም ተከትሎ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነጥቡን ወደ 32 ከፍ በማድረግ ዳግም መሪነቱን ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ መረከብ ችሏል። ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የፕሪሚየር ሊጉ መሪነትን ሲጨብጥ በሶስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ሰኔ 23 ቀን 2011 ዓ.ም መካሄድ የነበረበት ቢሆንም በአማራ ክልል በተከሰተው ወቅታዊ ሁኔታ ምክንያት የክልሉ የስፖርት ኮሚሽን የጨዋታው መርሃ ግብር እንዲራዘም ለኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፌዴሬሽን ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ለአንድ ሳምንት መራዘሙ የሚታወስ ነው። የአንድ ሳምንት መርሃ ግብር በቀረው የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ በመርሃ ግብሩ መሰረት ሁሉንም የሊጉን ጨዋታዎች አድርጓል። በ31 ነጥብ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ቀሪ አንድ ጨዋታውን ዱራሜ ላይ ከምባታ ዱራሜን የሚገጥም ሲሆን፤ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ተጋጣሚውን ካሸነፈ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ መሆኑን ያረጋግጣል። በአንጻሩ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ ለመሆን የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ማሸነፍ ወይም አቻ በመውጣት አሁን ባለው ሁኔታ ቂርቆስ በግብ ክፍያ ስለሚበልጥ አሸናፊ የመሆን እድል ይኖረዋል። የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻ 20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሐምሌ 6 እና 7 ቀን 2011 ዓ.ም የሚካሄዱ ይሆናል። ድሬዳዋ ከተማ በፋይናንስ ችግር ቡታጅራ ከተማ በጨዋታዎች ላይ በተደጋጋሚ ባለመገኘት የፎርፌ ውጤት እየተሰጠበት በመሆኑ ምክንያት ከውድድሩ ውጪ መሆኑ ይታወሳል። በዚህም ምክንያት በፕሪሚየር ሊጉ ተሳታፊ የሆኑ ክለቦች ቁጥር ወደ ስምንት ዝቅ ብሏል። የኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ዘንድሮ ሲካሄድ ለሶስተኛ ጊዜ ነው። ፕሪሚየር ሊጉ በ2009 ዓ.ም ሲጀመር መከላከያ የመጀመሪያ አሸናፊ የነበረ ሲሆን፤ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ የአምናው የፕሪሚየር ሊጉ አሸናፊ እንደነበር የሚታወስ ነው።