የፖለቲካ አለመረጋጋት በዩኒቨርሲቲዎች መማር ማስተማር ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል- ዩኒቨርሲቲዎች - ኢዜአ አማርኛ
የፖለቲካ አለመረጋጋት በዩኒቨርሲቲዎች መማር ማስተማር ላይ ተጽዕኖ ፈጥሯል- ዩኒቨርሲቲዎች

ሰኔ 30/2011 በተጠናቀቀው የትምህርት ዘመን ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራን ቢጀምሩም በመጀመሪያው ወሰነ ትምህርት ማገባደጃ እና በሌሎችም ጊዜያት ግጭቶች ማስተናገዳችውን ዩኒቨርሲቲዎች ገልጸዋል።
ተማሪዎቹ የብሔር መልክ የያዘ ግጭት ውስጥ ገብተው ነበር ያሉት የአምቦ ዩኒቨርሲቲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት አስተባባሪ አቶ ሙለታ ዱጉማ፤ በትምህርት ዘመኑ አጋማሽና ማብቂያ የመማር ማስተማር ሥራ መስተጓጎሉን ተናግረዋል።
በህዳር ወር ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የዜጎችን መፈናቀል መነሻ በማድረግና በታህሳስ አጋማሽ ደግሞ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የተከሰቱ ግጭቶችን ተከትሎ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ሁከት መፈጠሩንም ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው በዚህ ወር መጀመሪያ ጀምሮ የብሔር መልክ የያዘ ግጭት ተከስቶ፤ በርካታ ተማሪዎች መጎዳታቸውንና የአንድ ተማሪ ህይወት ማለፉን የተናገሩት አቶ ሙለታ፤ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ በተለይ በአማራና በኦሮሞ ተማሪዎች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ብዙ ጊዜ መሞከሩንና በግጭቶችም ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።
በግጭቱ ምክንያት የባከኑ የትምህርት ጊዜን፤ተጨማሪ ማካካሻ ግዜ በመመደብ በአሁኑ ወቅት የማጠናቀቂያ ፈተና በመሰጠት ላይ ነውም ብለዋል።
ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ በ2011 የትምህርት ዘመን ከተማሪዎች ቅበላ ጀምሮ በሰላማዊ መንገድ እያስተማረ ቢቀጥልም በመሃል ፈታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውታል።
በዩኒቨርሲቲው የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬከተር አቶ ደሳለው ጌትነት እንዳሉት በትምህርት ዘመኑ የተማሪዎች ስነምግባር ግንባታ ላይ እና ሰላማዊ የመማር ማስተማርን ለማስቀጠል ሥራዎች ሲሰሩ ነበር።
በሂደት ግን በሀገሪቱ ያለው ፖለቲካዊ አለመረጋጋትን ተከትሎ በህዳር ወር መጨረሻ እና በግንቦት ወር ሁለት የፀጥታ ችግሮች ማጋጠማቸውንም ጠቅሰው፤ ህዳር ላይ የተከሰተው አለመረጋጋት ወዲያውኑ የቆመ ቢሆንም በግንቦት ወር የተከሰተው ችግር የአንድ ተማሪ ህይወትን መቅጠፉን ተናግረዋል።
“የግንቦቱ ክስተት በዩኒቨርሲቲው ታሪክ አስቀያሚው ነው” የሚሉት አቶ ደሳለው፤ጎበዝ ተማሪዎችን ታላሚ ያደረገ ጥቃት እንደተፈጸመም ነው ያነሱት።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሪት መቅደስ ተስፋሁን በበኩላቸው በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የታዩ ግጭቶች በድሬዳዋም መታየቱን ተናግረው፤ ግንቦት ወር ላይ የእግር ኳስ ክለብ ጨዋታና ሃይማኖትን መነሻ ያደረጉ ግጭቶች ጉዳት ማስከተላቸውን ነው የገለጹት።
በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የግለሰቦች ወይም የጥቂት ቡድን ጸብን ወደ ብሔር መልክ የመቀየር አዝማሚያ መስተዋሉን ተናግረዋል።
አምቦ ዩኒቨርሲቲ ወደ ብሔር ግጭት የገቡት ተማሪዎችን ሰብስቦ ተወካዮቻቸውን በመምረጥ፣ ከምዕራብ ሸዋ አስተዳደር፣ ከአባገዳዎችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ተደጋጋሚ ምክክሮችን በማድረግ የማረጋጋት ሥራ መሰራቱን ነው አቶ ሙለታ የጠቀሱት።
“ዩኒቨርሲቲዎች የውጭ ፖለቲካ ንፋስ ተጠቂ ሆነዋል” የሚሉት አቶ ሙለታ፤ ተማሪዎችም ከውጭ የሚናፈሱ ፖለቲካ አዘል ተፅዕኖዎችን የማንጸባረቅ አዝማሚያ እንደሚያሳዩ ጠቁመዋል።
ተማሪዎች የሚናፈሱ መረጃዎችን እና ፖለቲካዊ ሁኔታዎችን መተንተንና መረዳት ላይ ብስለት አለማዳበራቸውም ለግጭትና ለጉዳት በር ከፋች መሆኑን ነው ያነሱት።
በአንድ ዩኒቨርሲቲ የሚነሳ ረብሻን ተከትሎ በሌላውም እየተከሰተ ነው ያሉት አቶ ደሳለው፤ ለአብነትም በህዳር ወር መጨረሻ የተከሰተው አለረጋጋት በሌላ ዩኒቨርሲቲ ከተከሰተ ግጭት ጋር የተገናኘ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህ ዓመት የስነምግባር ስልጠናዎችን በመስጠትና ከተማሪዎች ጋር ምክክር በማድረግ ብዙ ሊፈጠሩ የሚችሉ ግጭቶችን መከላከል መቻሉን ነው የገለጹት።
ወይዘሪት መቅደስ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የተባረሩ ተማሪዎችን ከግቢ እንዲወጡ በማድረግ፣ አገልግሎት አሰጣጥ እንዳይጓደል፣ ትምህርት በአግባቡ እንዲሰጥ፣ ተማሪዎች ጥያቄያቸውን በሰላማዊ ሁኔታ እንዲያቀርቡ ጥረት ቢያደርግም ችግር ተከስቷል።
በሀገሪቱ የዜጎች መፈናቀልና መሞት ተማሪዎችን ተረጋግተው እንዳይማሩ ያደርጋቸዋል ያሉት አቶ ደሳለው፤ በማህበራዊ ሚዲያ የሚናፈሰው ወሬ ና በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ ቀውስ በመማር ማስተማር ላይ አሉታዊ ጫና ፈጥሯል ብለዋል።
በየዩኒቨርሲቲው ግጭት የሚቀሰቅሱ ግለሰቦችን አስቀድሞ መቆጣጠር እንደሚገባ የተናገሩት አቶ ሙለታ፤ አምቦ ዩኒቨርሲቲ በተጠናቀቀው የትምህርት ዘመን ሁለተኛ መንፈቅ ላይ ትምህርት ሲያስተጓጉሉ ነበር ያላቸውን 11 ተማሪዎችን ከትምህርት ማገዱንም ጠቁመዋል።
በተማሪዎች መካከል የመቻቻል እሴትን የማስተማር ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ጠቁመው፤ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ሲመለሱ የሰላም አምባሳደር እንዲሆኑ መስራት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።
ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ በማድረግ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ መከናወኑን የገለጹት ደግሞ በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂ ኮሙዩኒኬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ዘውዱ እምሩ ናቸው።
በታህሳስ ወር በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የታየው ችግር በባህርዳር ዩኒቨርሲቲም ስጋት ፈጥሮ ለአንድ ሳምንት ትምህርት ከመቋረጥ ውጭ በዓመቱ ምንም ዓይት የጸጥታ ችግር እንዳላጋጠማቸውም ገልጸዋል።
ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹ በማህበራዊ ሚዲያና በውጫዊ የፖለቲካ ተፅዕኖ እንዳይወድቁ፣ ምክንያታዊነትን የማጎልበት፣ ውይይቶችን በተደጋጋሚ በማካሄዱና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር የመስራት ልምድ በማዳበሩ የመማር ማስተማሩ ሰላማዊ እንደነበረም አንስተዋል።