ቀጥታ፡

አዲሱ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ረቂቅ ህግ ችግሮችን በተቀናጀ አሰራር ለመፍታት ያስችላል ተባለ

ሰኔ 29/2011 የሚሻሻለው የኢንቨስትመንት ረቂቅ ህግ በኢንቨስትመንት አሰራር ችግሮችን በተቀናጀ መልኩ ለመቅረፍ እንደሚያስችል የረቂቅ ህጉ ማሻሻያ አባላት ተናጋሩ። ከአራት ወራት በፊት ጀምሮ ዝግጅቱ የተጀመረው አዲሱ የኢንቨስትመንት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተከታታይ ውይይት እየተደረገበት ነው። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከህግ ባለሙያዎች፣ ከውጭና ከአገር ውስጥ የልማት አጋሮች ጋር ዛሬ ባደረገው ውይይት ላይ እንደተባለው፤ አዲሱ ሕግ በኢንቨስትመንት ላይ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮችን በተቀናጀ መንገድ ለመፍታት ያስችላል። የረቂቅ ሕጉ ዝግጅት ባልደረባ ዶክተር ታደሰ ካሳ የወቅቱ አለም አቀፋዊ ሁኔታዎች፣ ወቅታዊ የመንግስት የኢኮኖሚ ማሻሻያ አቅጣጫዎች ነባራዊ ሁኔታዎች ከዚህ በፊት የነበረው አዋጅ ለአምስተኛ ጊዜ እንዲሻሻል እንዳስገደዱት ገልጸዋል። ረቂቅ አዋጁ በፌዴራልና በክልል ኢንቨስትመንት ባለድርሻ አካላት ያላቸውን ስልጣንና ድርሻ በግልጽ የሚያስቀምጥ፣ በቅንጅት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል። ይህም በውጭና በአገር ውስጥ ኢንቨስተሮች ላይ ይደርስባቸው የነበረውን መጓተትና የመግባባት ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያግዝ ተናግረዋል። የህግ ባለሙያና ጠበቃ አቶ ታምሩ ወንድምአገኘሁ “ህጉን አውጥቶ ከህጉ ጋር የሚሄድ የአፈጻጸም ስርዓት መዘርጋት እንደሚገባና በየደረጃው ያሉ አስፈጻሚዎች ኢንቨስተሮችን የሚረዱ እንጂ ሞጋች መሆን የለባቸውም” ብለዋል። የአገሪቱ ኢንቨስትመንት ድክመቱ የህግ ክፍተት ብቻ ሳይሆን በጥቂቶች በተረቀቀ ህግ በማተኮር ተፈጻሚነቱን በሚወስኑ አካላት ተሳትፎ ያለመዘጋጀቱም ጭምር እንደሆነ ጠቁመዋል። ረቂቅ አዋጁ የአገሪቱን ያለፉት ዓመታት የታክስ፣ የቅንጅት፣ የቀጠሮ አሰጣጥ ችግሮችን መፍታት የሚያስችሉ ድንጋጌዎች እንደተካተቱበት ገልጸው፤ በየደረጃው የሚገኙ አስፈጻሚዎች ላይ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲመጣ መሰራት እንዳለበትም ገልጸዋል በቀጣይም በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በረቂቁ ላይ ውይይት የሚካሄድ ሲሆን አዋጁ በ2012 የበጀት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። የረቂቅ ህግ ዝግጅቱ ከግሉ የኢንቨስትመንት ዘርፎች የተካተቱበት ዘጠኝ አባላት ያሉትና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ቦርድ የሚመራ ሲሆን ህጉ አካታችና አስቻይ ሊሆን እንደሚችል ታምኖበታል። ኢትዮጵያ ከ28 ዓመታት በፊት ካወጣችው ከመጀመሪያው የኢንቨስትመንት ህግ በኋላ አዋጆቿን ስታሻሻል የአሁን ለአምስተኛ ጊዜ ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም