ቀጥታ፡

የምሥራቅ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ለአገራዊ ለውጥ ቀጣይነት የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ ድርሻቸውን እንደሚወጡ ገለጹ

ሰኔ 29/2011 ለአገራዊ ለውጥ ቀጣይነት የአካባቢያቸውን ሰላም በማስጠበቅ ድርሻቸውን እንደሚወጡ የምሥራቅ ወለጋ ዞን የሰላምና ልማት ኮንፍረንስ ተሳታፊዎች ገለጹ። የዞኑን ሕዝብ በመወከል ትናንት በነቀምቴ ከተማ የተወያዩት የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደተናገሩት የአካባቢያቸውን ሰላም ጸጥታ በማስከበር ለለውጡ ቀጣይነት ይሰራሉ። የሐሮ ሊሙ ወረዳ ተሳታፊ አባ ገዳ ነገሱ ደያስ በሰጡት አስተያየት በኅብረተሰቡ ዘንድ የነበረውን ሰላም የማስጠበቅ ሥራ የፀጥታ አካሉና የአመራሩ አድርጎ የመመልከት አስተሳሰብ በማስተካከል ተሳትፎአቸውን እንደሚያሳድጉ አስረድተዋል። ኅብረተሰቡ በየአካባቢው የሚፈጠረውን የፀጥታ ችግር በመከታተልና መረጃ ለፀጥታ አካሉ መስጠት እንዳለበትም አመልክተዋል። ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን በማራመድ የሕዝቡን ሰላምና ፀጥታ የሚያደፈርሱ ኃይሎችን በመከታተል ለሕግ በማቅረብ ድርሻቸው ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። የወማ አጋሎ ወረዳ ተሳታፊ አቶ ተመስጌን ጉተታ በበኩላቸው የኅብረተሰቡ ሰላም የሚጠበቀው የሕግ የበላይነት ሲረጋገጥ  መሆኑን ገልጸው፣ መንግሥት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የጀመረውን እንቅስቃሴ በመደገፍ እንደሚንቀሳቀሱ አስታውቀዋል። መንግሥት ግንባታቸው ያልተጠናቀቁና የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦላቸው ግንባታቸው ያልተጀመሩ  ፕሮጀክቶች ለመገንባት ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል። የድጋ ወረዳው አቶ ታምሩ ሹሼ በበኩላቸው  ኦነግ ሸኔ  በሚል ስያሜ የሚንቀሳቀሰው ቡድን ከሕገ ወጥ እንቅስቃሴ በመውጣት ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲገባ አሳስበዋል። በሰላም፣ በአንድነት፣ በፍቅር፣ በመቻቻል፣ በመከባበርና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዘመን በጠመንጃ ኃይል የፖለቲካ አጀንዳቸውን የሚያራምዱ ኃይሎችን  አሳልፌ ለሕግ ለማቅረብ  ድርሻዬን እወጣለሁ ብለዋል። የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳምሶን ቢራቱ መንግሥት  የዜጎችን ሰላም  ለማረጋገጥና  የሕግ  የበላይነት  ለማሰከበር  እያከናወነ  ላለው ተግባር ሕዝቡ ከጎኑ መቆም እንዳለበት አሳስበዋል። በዘር፣በሃይማኖት፣በቋንቋ ሳይከፋፈሉ የሕግ የበላይነትን ለማስበርና ሰላምና መረጋጋት መፍጠር   እንደሚያስፈልግ  አስታውቀዋል። በኮንፍረንስ ከ18 ወረዳዎች የተውጣጡ ወጣቶች፣አባ ገዳዎች፣ሴቶች፣በየደረጃው የሚገኙ አመራሮችን ጨምሮ ከ1 ሺህ 200 በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም