ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና ሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ማሻሻያ ረቂቅ ሰነድ ላይ ውይይት እየተደረገ ነው

ሰኔ 29/2011 የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና ሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሀገሪቷ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ሚናና ተቀባይነት ታሳቢ ባደረገ መንገድ እየተሻሻለ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ክልላዊ ነባራዊ ሁኔታዎች እየተለዋወጡ መምጣታቸው እንዲሁም በነባሩ ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይ አላስፈላጊ ዝርዝሮች መካተታቸው ለፖሊሲው መሻሻል በምክንያትነት ተነስተዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚሻሻለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ዙሪያ ከሲቪክ ማህበራትና ከምሁራን ጋር ውይይት እያደረገ ነው። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና ሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2002 የወጣ ቢሆንም ከለውጡ እና ከዓለም ነባራዊ ሁኔታው ጋር አብረው የማይሄዱ ጉዳዮች አሉት ተብሏል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ማርቆስ ተክሌ እንዳሉት፤ ፖሊሲው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ፣ በአህጉርና በክልል ደረጃ ያላትን ሚና ታሳቢ ያደረገ ነው። የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መነሻው አሁንም ከውስጥ ወደ ውጭ እንደሆነ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የመጣው ለውጥ በፖሊሲው ላይ አሉታዊ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል። በመሆኑም ከአገሮች ጋር ይሄን የሚመስል ግንኙነት ይኖረናል፤ ይህ መሆን አለበት" የሚሉ ዝርዝር ሁኔታዎች ተወግደው ከሀገራዊ ለውጡ ጋር ተመጋጋቢ ማሻሻያዎች ተካተውበታል ብለዋል። ለኢትዮጵያ በባለብዙ ወገን ግንኙነትን በሚያጎላ መንገድ ክልላዊ ትስስርና ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲ መፍጠርም አላማው ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ህዝብ እያላት ወደብ አልባ የሆነች ሀገር በመሆኗ ያለ ሶስትኛ ወገን ጣልቃ ገብነት የወደብና ባህር ሃይል አገልግሎት እንድታገኝ ማድረግም የፖሊሲው አካል መሆኑን አስረድተዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ውጭ ግንኙነት መምህር ፕሮፌሰር ካሳሁን ብርሃኑ ፖሊሲው የጎረቤት ሀገሮችን ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑን ገልጸዋል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና ሀገራዊ ደህንነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ሲወጣ ደቡብ ሱዳን ሉዓላዊት አገር ያልነበረች መሆኑ፤ ከሶማሊያና ኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነትም እንደገና መታየት ያለበት መሆኑንም በማከል። በተጨማሪም የሚሻሻለው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታዩ የትብብር ለውጦች እንዲሁም ዲያስፖራዎችን ግምት ውስጥ ያስገባ እንዲሆን መደረጉንም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም