የሀሳብ ልዩነትን ለመፍታት ብቸኛው አማራጭ ውይይት መሆን አለበት- የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የሀሳብ ልዩነትን ለመፍታት ብቸኛው አማራጭ ውይይት መሆን አለበት- የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች
ሀዋሳ ሰኔ 29/ 2011 ለአገር ሰላምና ለህዝብ ደህንነት ሲባል የሀሳብ ልዩነቶችን ለማስታረቅ ብቸኛው አማራጭ ውይይት መሆን እንዳለበት የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ። ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማው አንዳንድ ነዋሪዎቹ እንዳሉት የመነጋገር ባህልን በማዳበር የሐሳብ ልዕልና የበላይነት እንዲይዝ ማድረግ የዘመናዊነትና የሥልጣኔ ምልክት ነው። መንግሥት በችግሮች ዙሪያ ፊት ለፊት በመነጋገር የጋራ ስምምነት የሚደረሰባቸው መድረኮች ማዘጋጀት እንዳለበትም አመልክተዋል። በከተማዋ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ በላይሁን ታሪኩ እንዳሉት በልዩነቶቻችን ላይ የመነጋገርና የመወያየት ባህል እንዲጎለብት መሥራት ያስፈልጋል ይላሉ። በመድረኮች ''የኔ ትክክል ነው'' ባዩ እየበዛ እድማጭ የሌለበት ሁኔታ እየተስተዋለ መምጣቱንና ይህም ሳቢያ ልዩነቶች እየሰፉና ቂምና ጥላቻ እየገነነ መምጣቱን ያስረዱት አስተያየት ሰጪ፣የመደማመጥ ባህልን ማጎልበት አስፈላጊ መሆኑንም ይመክራሉ። ''ሁላችንም የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመፍታት ከውይይት ይልቅ ኃይልና ጉልበትን መጠቀም መፍትሄ ማድረጋችን በቅርቡ በባህር ዳር የተከሰተው ችግር ማሳያ ነው'' ብለዋል። ልጆችን ስናሳድግ አቅርቦ በመምከርና በማስተማር ከመመለስ ቁጣና ዱላን መጠቀማችን በአስተዳደጋቸው ላይ ያሳደረው ተጽእኖ በኃይል የማመን ዝንባሌ ምክንያት መሆኑም አቶ በላይነህ አስረድተዋል። በዚሁ ክፍለ ከተማ የፊላደልፊያ ቀበሌ ነዋሪዋ አቶ አብርሀም ሸዋልኡል በበኩላቸው ግጭት በበረታባቸው አገሮች የምናየው የእርስ በእርስ ጦርነትና ግጭት እርስ በእርስ ከመነጋገር ይልቅ፤ኃይል እንደ መፍትሄ በመቅረቡ መሆኑን ገልጸዋል። መንግሥት የውይይት መድረኮችን እስከ ቀበሌ ድረስ በማድረግ ሕዝቡን መስማት እንዳለበት ተናግረዋል። በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩ መገናኛ ብዙኃን ሕዝብን የሚያስተላልፏቸው መልዕክት ቁጥጥር እንዲደረግባቸውም ጠይቀዋል። የምስራቅ ክፍለ ከተማ ውቅሮ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ታደለ አዳነ በሰጡት አስተያየት የሐሳብ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት እየቻልን "የማይሽር ጥላቻን መጋበዝ" ተገቢ አይደለም ብለዋል። ምሁራንና የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚሳተፉባቸው መድረኮች በመፍጠር የሐሳብ ልዕልና እንዲነግስ መሰራት እንዳለበት አመልክተዋል።