ቀጥታ፡

ሀገራዊ ለውጡን ለማጠናከርና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ድጋፋችንን እንቀጥላለን...የኢሉአባቦር ዞን ነዋሪዎች

ሰኔ 29/2011 በሁሉም መስክ የሚደረገውን ሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ለማጠናከርና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ የኢሉአባቦር ዞን ነዋሪዎች ገለጹ። የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች በበኩላቸው የህግ የበላይነትን የሚፈታተኑ ተግባራትን ሲከሰቱ መንግስት ፈጣን እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል መቱና አምቦ ከተሞች የሰላምና የልማት ኮንፈረንሶች ተካሂዷል። በመቱ ከተማ በተካሄደ ኮንፈረንስ ላይ ከኢሉአባቦር ዞን 13 ወረዳዎች የተወጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል። በኮንፈራንሱ ላይ ነዋሪዎቹ እንዳሉት ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በሀገሪቱ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ በሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ላይ መሻሻሎች እንዲኖሩና የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነፃነት እንዲረጋገጥ አድርጓል:: አስተያየታቸውን ከሰጡት የመቱ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ጫንያለው ለሙ ከለውጡ ወዲህ ዜጎች ሀሳባቸውን በነፃነት እንዲገልፁና በሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዲሳተፉ መደረጉ ለዲሞክራሲ መጎልበት አስተዋፅዎ እንዳለው ተናግረዋል:: “መንግስት በትጥቅ ትግልና በእስር ላይ ለነበሩ ዜጎች ይቅርታ በማድረግ ለለውጡ ቀጣይነት የበኩላቸውን እንዲወጡ ቢያደርግም አንዳንዶቹ ተመልሰው ለውጡን ለማደናቀፍ መሞከራቸው አሳዛኝ ነው” ብለዋል። መንግስት ለውጡን ለማደናቀፍና የህብረተሰቡን ሰላም በሚያውኩ ላይ ፈጣንና ተገቢ እርምጃ እንዲወስድ የጠየቁት አቶ ጫን ያለው የህግ የበላይነትንና ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል:: በመንግስት የይቅርታ፣ የፍቅርና የመደመር መርህ ሀገራዊ አንድነትና ፍቅር እየጎለበተ ቢመጣም ለውጡን በሚያደናቅፉ አካላት ሰላም እንዳይጠፋ መንግስት የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ በኩል በትኩረት እንዲሰራ የጠየቁት ደግሞ አቶ ገዛኸኝ ዳባ የተባሉ የኮንፈረንሱ ተሳታፊ ናቸው:: " ይቅርታና ፍቅር ለቀጣይ የጋራ መግባባትና አንድነት ወሳኝ ቢሆንም አጥፊዎች ደግሞ በህግ ሊጠየቁ ይገባል" ብለዋል:: በዞኑ ከሚገኙ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ፍቅርና አንድነታቸውን በማጠናከር ለለውጡ ስኬትና አስተማማኝ ሰላም መስፈን የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል:: የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ግርማ ረጋሳ በበኩላቸው “በክልሉ ከለውጡ ወዲህ በፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስኮች ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች ቢኖሩም ለውጡን ወደ ኋላ ለመመለስ በሚፈልጉ አካላት በአንዳንድ አካባቢዎች አልፎ አልፎ የሰላም መደፍረስ ይስተዋላል” ብለዋል:: መንግስት አጥፊዎችን በመከታተል የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ህብረተሰቡ የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ ሀገራዊ ለውጡን አጠናክሮ በማስቀጠል በኩል የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል:: “ህብረተሰቡ ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ወንድሞቹ ጋር ያለውን ፍቅርና አንድነት በማጠናከር ኢኮኖሚውንና ልማትና ለማሳደገ በሚደረግ ጥረት የለውጥ ኃይል መሆን አለበት” ብለዋል:: በኮንፍራንሱ ላይ ከዞኑ 13 ወረዳዎች የተወጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል:: በተመሳሳይ ዜና ሰላምን በዘላቂነት ማረጋገጥና ልማትን ማስቀጠል ላይ ያተከረ ኮንፈረንስ ትናንት በአምቦ ከተማ ተካሂዳል። በመድረኩ የተሳተፉት የአምቦ ከተማ ነዋሪዎች በእዚህ ወቅት እንዳሉት የህግ የበላይነትንና የህዝብ አንድነትን የሚፈታተኑ ተግባራት ሲከሰቱ በመንግስት በኩል አፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል። ተሳታፊዎች መካከል አቶ መገርሳ ጉሊቲ በሰጡት አስተያየት ለሀገራዊ የለውጥ እንቅስቃሴ የለሰላም መጠናከር ወሳኝ በመሆኑ የአካባቢያቸውን ሰላም በመጠበቅና ልማትን በማስቀጠል ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ ተናግረዋል፡፡ ልማትንም ሆነ ሰላምን ማስቀጠል የሚቻለው የህግ የበላይነት ሲረጋገጥ በመሆኑ መንግስት ሳይዘናጋ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ህግን እንዲያስከብር ጠይቀዋል። በሀገሪቱ የተጀመረው የልማትና የለውጥ ጉዞ ቀጣይነት ኖሮት ውጤታማ እንዲሆን የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ የድርሻውን እንደሚወጣ የገለጸው ደግሞ ወጣት ቢፍቱ ሙለታ ነው፡፡ የሀገር ሽማግሌው አቶ አበበ ነገዎ በበኩላቸው የህግ የበላይነትንና የህዝብ አንድነትን የሚፈታተኑ ተግባራት ሲከሰቱ መንግስት አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል። “መንግስት በተለይ የአገሪቱን ህዝቦች ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማስጠበቅ ፀረ-ሰላም የሆኑ ተግባራትን ጊዜ ሳይሰጥ በመከላከል ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት ይኖርበታል” ብለዋል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የአምቦ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ተረፈ በዳዳ በበኩላቸው የመድረኩ ዓላማ ሰላምና ልማትን አጠናክሮ በማስቀጠል በኩል የህብረተሰቡና የመንግስት ሚና ለይቶ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ መሆኑን ተናግረዋል። የተጀመረው አገራዊ ለውጥ ለማስቀጠልና የህግ የበላይነትን ለማስቀጠል ህብረተሰቡና መንግስት እንዴት ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸው በገራ ለመወያየት ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑንም አስረድተዋል። የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት አባል አቶ ሰለሞን መኮንን በዚሁ ጊዜ እንዳተናገሩት በመድረኩ በኦሮሚያ ክልል ሰላምንና የህግ የበላይነትን ማስከበር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ትኩረት ተደርጎ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ህብረተሰቡ ሀገራዊ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ አካላትን ለማጋለጥና ለመታገል የጀመረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ “የብዙ ወጣቶች ሕይወት አልፎ የመጣውን ሀገራዊ ለውጥ በመጠበቅ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በትኩረት እየተሰራ በመሆኑ ህብረተሰቡ በአሉባልተኖች ውሸት ሳይታለል ለቆመለት አላማ ጠናክሮ መስራት ይኖርበታል” ሲሉም አሳስበዋል፡፡ በመጨረሻም የመድረኩ ተሳታፊዎች ለውጡን ለማደናቀፍ በተለያዩ አካላት የሚደረጉ ሙከራዎችን በማክሸፍና በማጋለጥ እንደሚሰሩ የጋራ መግባባት ላይ በመድረስ ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ በመውጣት ኮንፈረንሱ ተጠናቆአል፡፡ በመቱና በአምቦ ከተሞች በተካሄደ የሰላምና የልማት ኮንፈረንሶች የከተማ አመራሮች፣ የወጣት አደረጃጀት መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች መሳተፋቸው ታውቋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም