በደቡብ ክልል ሕገ-ወጥ ንግድ፣ የመድኃኒትና ምግብ ዝውውር በስፋት እንደሚስተዋል ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ክልል ሕገ-ወጥ ንግድ፣ የመድኃኒትና ምግብ ዝውውር በስፋት እንደሚስተዋል ተገለጸ
ሰኔ 28/2011 በደቡብ ክልል ሕገ-ወጥ ንግድ፣ የመድኃኒትና ምግብ ዝውውር በስፋት እንደሚስተዋል የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ደቡብ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። ጽሕፈት ቤቱ ባደረገው የክትትል ሥራዎች መለየቱን ተናግሯል፡፡ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ከደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ላይ ያተኮረ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂደዋል ፡፡ በባለስልጣኑ ደቡብ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ቡድን መሪአቶ ፍቃዱ ንማኔ እንደገለጹት በክልሉ ህገ ወጥ ንግድ፣ የመድኃኒትና ምግብ ዝውውር በስፋት ይስተዋላል። በኮንትሮባንድ ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው በህብረተሰቡ ጤናና ምጣኔ ሀብት ላይ ጉዳት እያስከተሉ የሚገኙ መድኃኒቶች በስፋት ገበያ ላይ እንደሚዘዋወሩ አስረድተዋል። የተለያዩ መድኃኒቶች ከመንግስት ጤና ተቋማት ተሰርቀው እየወጡ በግል ተቋማት እየተሸጡ መሆናቸውን በተሰሩ የክትትል ስራዎች መረጋገጡን አስረድቷል። የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው የታሸጉ ምግቦችና መድኃኒቶች በንግድ ቤቶችና በጤና ተቋማት ለተጠቃሚዎች እየቀረቡ መሆኑንም ጠቁመዋል። ለምግብነት የሚውሉት ቅቤ፣ ማርና በርበሬ ከባዕድ ነገር ጋር ተቀላቅለው ለገበያ እየቀረቡ መሆናቸውንም አመልክተዋል። በህገ ወጥ ተባራት ላይ በተሰማሩ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃዎች መወሰዳቸውን የገለጹት ቡድን መሪው በእዚህም 14 የግል የጤና ተቋማት ፈቃዳቸው ሲታገድ 25 ተቋማት ደግሞ ማስጠንቀቂ እንደተሰጣቸው አስረድተዋል። በግለሰቦች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለማስወሰድ የክስ መዝገቦች መከፈታቸውንም ጠቁመዋል። የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ በድሉ ቁጮ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራር ልል መሆንና በችግሩ ግዝፈትና ጥልቀት ልክ ህጋዊ እርምጃ አለመውሰድ ለታየው ክፍተት አስተዋፅኦ ማበርከቱን አስረድተዋል ፡፡ በሕገ-ወጥ የመድኃኒት ዝውውርና ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች ባለሀብቶች መሆናቸውን ያስረዱት አቶ በድሉ"ይሄም በሙስናና በተለያዩ ስልቶች አስፈፃሚ አካላት ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር የክስ ሂደቶች ተድበስብሰው አንዲቀሩ እያደረገ ነው" ብለዋል። በችግሩ ላይ ከሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶች ጋር ተቀራርቦ አለመስራት ችግሩ በተፈለገው ልክ እንዳይፈታ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል። የጌዴኦ ዞን ሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ መስከረም አታራ በበኩላቸው ዞኑ በሞያሌ በኩል ኢትዮጵን ከኬንያ ጋር በሚያገናኘው ዋና መስመ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ከፍተኛ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ እንደሚታይበት ተናግረዋል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሥራቸውን በተናጥል ሲያከናውኑ መቆየታቸውም ለታየው ደካማ አፈፃፀም አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል። የሲዳማ ዞን ወጣቶች ሊግ የከተማ ዘርፍ ኃላፊ መስፍን ከበደ ህገወጥ ስራውን የመከላከሉ ስራ ወጣቱን በስፋት ያካተተ እንዳልነበር ጠቁሟል። በተያዘው የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ህገ ወጥ ስራውን የመከላከል ተግባር ላይ ወጣቶችን በስፋት ለማሳተፍ እንቅስቃሴ መጀመሩንም አስረድቷል ፡፡ በሻሸመኔ ከተማ በተካሄደው የውይይት መድረክ ከክልልና ከዞኖች የተውጣጡ የሴቶችና ወጣቶች አደረጃጀቶች ተሳትፈዋል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡