የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የእግር ኳስ ውድድር እራሱን አገለለ - ኢዜአ አማርኛ
የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የእግር ኳስ ውድድር እራሱን አገለለ
ሰኔ 28/2011 የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ለመጠናቀቅ የአንድ ሳምንት ጨዋታ ብቻ ከቀረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የእግር ኳስ ውድድር እራሱን ማግለሉን አስታውቋል። ክለቡ ባለፈው የ29ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ከፋሲል ከነማ ጋር የነበረውን ጨዋታ ወደጎንደር በማቅናት ባለመጫወቱ ለፋሲል ከነማ ፎርፌ ተሰጥቷል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታውን ያላካሄደው በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ባለፈው ሰኔ 15/2011 ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ሳይካሄድ የቀረው ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ጋር የነበረውን አንድ ተስተካካይ ጨዋታ በቅድሚያ ማካሄድ አለብኝ በሚል ነው። ክለቡ 'የ28ኛ ሳምንት ጨዋታ ሳላደረግ የቀጣዩን ሳምንት ጨዋታ እንዳደረግ መወሰኑ ትክክለኛ አይደለም፤ ፎርፌ መሰጠቱም ፍትሃዊ አይደለም' በሚል ቅሬታውን ገልጿል። እነዚህ ፍትሃዊ ያልሆኑ ውሳኔዎች ፌዴሬሽኑ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ካለው የተዛባና አድሎዊ አመለካከት የመጡ ናቸው ሲልም ማህበሩ ወቀሳውን ሰንዝሯል። በመሆኑም ክለቡ ከፋሲል ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ የተሰጠው ፎርፌ ተነስቶ ፍትሃዊ ውሳኔ እስካልተሰጠ ድረስ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፕሪሚሪሊግ ውድድር እራሱን ማገለሉን ማህበሩ ገልጿል። ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ኮለኔል አዎል አብዱራሂም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ ጋር የነበረውንጨዋታ በመርሃ ግብሩ መሰረት ማካሄድ ነበረበት፤ ሆኖም ክለቡ በራሱ ፍቃድ ነው ጨዋታውን ያራዘመው ብለዋል። ጨዋታው በሚካሄድበት ሳምንት ተከስቶ ከነበረው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በከተማዋ ብዙ ህዝብ የሚሰብበሰብብት ሁኔታ ተከልክሎ ስለነበር ቡድኖቹ ጨዋታውን አዲስ አበባ ካደረጉ በዝግ ስለሚሆንና እንደ አማራጭ በክፍት ሜዳ መጫወት ከፈለጉ ደግሞ ከመዲናዋ ውጭ ማድረግ የሚችሉበት እድል ነበራቸው ሲሉ ኮሎኔል አወል ተናግረዋል። ለዚህም ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበት ራሱ ክለቡ ነው በማለትም አክለዋል። የ29ኛ ሳምንት ጨዋታውንም ወደ ጎንደር በማቅናት ከፋሲል ከተማ ጋር ማካሄድ የነበረበት ቢሆንም ክለቡ ይህንን ባለማድረጉ በመመሪያው መሰረት ፎርፌ ለፋሲል ከተማ ተስጥቷል ብለዋል። የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሊጠናቀቅ የአንድ ሳምንት ጨዋታ ብቻ የቀረው ሲሆን መሪነቱንም ፋሲል ከተማና መቐለ ሰባ እንድርታ በእኩል በ56 ነጥብ በጎል ክፍያ ተበላልጠው አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደየቅደም ተከተላቸው የተቀመጡ ሲሆን ሲዳማ ቡና ደግሞ በ54 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ 27 ጨዋታዎችን አድርጎ በ46 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።