ቀጥታ፡

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ሰራተኞች ደም ለገሱ

ሰኔ 27/2011 የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ሰራተኞች “ለወገን ደራሽ ወገን ነው” በሚል እሳቤ የደም ልገሳ አደረጉ። የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ይድነቃቸው ወርቁ ተቋሙ ይህንን የደም ልገሳ ተግባር ሲያከናውን ለአምስተኛ ጊዜ መሆኑን ጠቅሰዋል። የዘንድሮውን ለየት የሚያደርገው ባለፈው ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በአማራ ብሄራዊ ክልልና በአዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት በማውገዝ  መሆኑን ገልጸዋል። በዛሬው እለት ከ100 በላይ የተቋሙ ሰራተኞች ያደረጉት የደም ልገሳ የተከናወነው በወሊድና በአደጋ ምክንያት ህይወታቸውን እያጡ ያሉ ዜጎች በመታደግ አጋርነታችንን ለማሳየት ነው ሲሉም  ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። የደም ልገሳ ተግባሩ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶክተር አብይ አህመድ በተቋሙ ሲሰሩ በነበረበት ወቅት ተቋሙ ውስጥ ያለውን የስራም ሆነ የማህበራዊ ተሳትፎ እንዲጠናከር ያደረጉትን ጥረት ለማስቀጠል መሆኑንም አክለዋል። በዚህም መሰረት የቋሙ ሰራተኞች የበጎ ተግባራቸውን በማጠናከር በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በብልሽት ምክንያት ያለስራ የተቀመጡ  ኮምፒውተሮችን በመጠገን ለመስጠት ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። የተቋሙ ሰራተኞች የደም ልገሳ በነገው እለትም ይቀጥላል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም