የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ገጥሞት የነበረው ችግር ተወግዶ ግንባታው እየተፋጠነ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ገጥሞት የነበረው ችግር ተወግዶ ግንባታው እየተፋጠነ መሆኑ ተገለጸ
ሰኔ 27/2011 የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የስራ አፈፃፃም ገጥሞት የነበረው ችግር ተወግዶ ግንባታው ጥራቱን በጠበቀ መልኩ በመከናወን ላይ መሆኑን የፕሮጀክቱ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ፅህፈት ቤቱ ለአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች "የሃገራችን ሚዲያ ለህዳሴ ግድባችን አንደበት ነው" የሚል መሪ ሃሳብ የጉብኝት ፕሮግራም አካሂዷል። የፕሮጀክቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ኤፍሬም ወልደኪዳን በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት ግድቡ ገጥሞት የነበረው ችግር ሙሉ ለሙሉ ተወግዶ ግንባታው በመከናወን ላይ ይገኛል። እንደ ኢንጅነር ኤፍሬም ገለፃ ግንባታ ወቅት ጥልቅ ሸለቆ ማጋጠሙ፣ የኮንትራት ማሻሻያ መደረጉ፣ ከዚህ በፊት የነበረው ኮንትራት የተጣበበ መሆኑ፣ በሜቴክ እየተከናወኑ የነበሩ ስራዎች መዘግየት ቀደም ሲል ያጋጠሙ ችግሮች ነበሩ። በመሆኑም እነዚህን ችገሮች ለመፍታት የማስተካከያ እርምጃ በውሰድ ከአምስት ኮንትራከተሮች ጋር ውል ተፈፅሟል ብለዋል። የውል ማሻሻል በተደረገባቸው ስራዎች ላይም ክፍያ በመፈፀም በፍጥነት ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል። በዚህም የሲቪል ስራዎች ዋናው ግድብ 80 በመቶ፣ የግድቡ የቀኝ ሃይል ማመንጫ ቤት ግንባታ 63 በመቶ፣ የግራ ሃይል ማመንጫ 74 በመቶ፣ የጎርፍ ማስተንፈሻ 96 በመቶ፣ የሳድል ዳም 66 በመቶና የስዊች ያርድ ስራዎች 66 በመቶ መከናወኑን ጠቅሰዋል። በኤሌክትሮ መካኒካል ስራውም በአዲስ ውል ለኮንትራክተሮች ቅድመ ክፍያ በመፈፀም ወደ ስራ በመግባት ለሃይል ለማመንጫ የሚገጠሙ ተርባይኖችን የመበየድ ስራ በመስራት አጠቃላይ ስራው ከ25 በመቶ ወደ 27 በመቶ በላይ ከፍ እንዲል ተደርጓል። በአሁኑ ወቅት የሲቪል ስራው 84 በመቶና የኤሌክትሮ መካኒካል ስራውም 28 በመቶ መከናወኑን ተናግረዋል። ለግድቡ ውሃ የሚሞላበት አካባቢ ከአጠቃላዩ እስካሁን ለመጀመሪያ የሃይል ማመንጫ እንዲውል 39 ሺህ ሄክታር መሬት የመመንጠር ስራ መከናወኑንም ገልጸዋል። በመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ስራም 6 ወረዳዎችና 17 ማዕከላት ተለይተው የትምህርት ቤቶች፣ የጤና ኬላዎች፣ የግብርና ማሰልጠኛዎች፣ የአስተዳዳር ቢሮዎች፣ መኖሪያ ቤቶችና የተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች አፈጻጸም 70 በመቶ ደርሷል ብለዋል። የግድቡ ግንባታ ደህንነቱ በፀጥታ መዋቅሩ አስተማማኝ ጥበቃ እየተደረገለት መሆኑም ተገልጿል። ለግድቡ ግታ ባለፉት 10 ወራት ብቻ ህበረተሰቡ ከሚያደርገው የአይነትና የቁሳቁስ ድጋፍ ባሻገር ከ860 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።