የቦክስ ክለቦች ውድድር የፍጻሜ ጨዋታዎች ተካሄዱ - ኢዜአ አማርኛ
የቦክስ ክለቦች ውድድር የፍጻሜ ጨዋታዎች ተካሄዱ
ሰኔ 27/2011በአራተኛው ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ዛሬ ሁለት የፍጻሜ ጨዋታዎች በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ተካሄዱ። በውድድሩ 55 ወንድ እና 14 ሴት ተወዳዳሪዎች እየተሳተፉ ሲሆን በወንዶች ከ49 እስከ 91 ኪሎ ግራም በሴቶች ደግሞ ከ48 እስከ 60 ኪሎ ግራም ፉክክር የሚደረግባቸው የክብደት ዘርፎች ናቸው። አዲስ አበባ ፖሊስ፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶች፣ ማራቶን፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚና ጎንደር ከተማ በውድድሩ እየተሳተፉ ያሉ ክለቦች ናቸው። የቦክስ ክለቦች ውድድር ትናንት በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የተጀመረ ሲሆን ዛሬ በውድድሩ ሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለት የፍጻሜ ጨዋታዎች ተካሄደዋል። በ91 ኪሎ ግራም ወንዶች የፌዴራል ፖሊስ ተወዳዳሪው ሙሉቀን መልኬ የድሬዳዋ ከነማ ተጋጣሚውን ሊበን መሐመድን በበቃኝ በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝቷል። በ51 ኪሎ ግራም ሴት የአዲስ አበባ ፖሊሷ ሮማን አሰፋ የጎንደር ከተማዋን ተወዳዳሪ የምስራች ተስፋዬን በነጥብ በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ አግኝታለች። ውጤቱንም ተከትሎ አዲስ አበባ ፖሊስ በውድድሩ ያገኛቸውን የወርቅ ሜዳሊያዎች ብዛት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል። ትናንት ውድድሩ ሲጀመር በ57 ኪሎ ግራም ሴቶች የአዲስ አበባ ፖሊስ ተወዳዳሪ የሆነችው ፈለቀች ሰይፋ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ተጋጣሚዋን ሀብታም ልዑልን በማሸነፍ ለክለቧ የወርቅ ሜዳሊያ ማስገኘቷ የሚታወስ ነው። ዛሬ ከተደረጉ የፍጻሜ ውድድሮች በተጨማሪ በወንዶች 52፣ 56፣ 60፣ 64 እና 75 ኪሎ ግራም በሴቶች በ48 እና በ54 ኪሎ ግራም የማጣሪያ ጨዋታዎች ተካሄደዋል። የብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ዋንኛ ዓላማ በነሐሴ ወር 2011 ዓ.ም በሞሮኮ ርዕሰ መዲና ራባት በሚደረገው 12ኛው የመላው አፍሪካ ጨዋታ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ተወዳዳሪዎችን መምረጥ እንደሆነ ከኢትዮጵያ ቦክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል። በአራት ዙር በሚካሄዱት ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር ያሉ ውጤቶች ተደምረው በሁለቱም ፆታዎች አጠቃላይ አሸናፊ እንደሚለይም ታውቋል። ዘንድሮ ሦስት ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድሮች በድሬዳዋ፣ በወላይታ ሶዶ እና በደሴ ከተሞች መካሄዳቸው የሚታወስ ነው። በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የተጀመረው አራተኛው ብሔራዊ የቦክስ ክለቦች ውድድር እስከ ሰኔ 29 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል።