ቦይንግ ኩባንያ በ737 ማክስ አውሮፕላን አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊያደርግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ቦይንግ ኩባንያ በ737 ማክስ አውሮፕላን አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ሊያደርግ ነው
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2011 ቦይንግ ኩባንያ 737 ማክስ 8 አውሮፕላኑ በኢትዮጵያ እና ኢንዶኔዥያው ባጋጠሙት አደጋዎች ህይወታቸውን ላጡ 346 ሰዎች ቤተሰቦችና ጉዳት ለደረሰባቸው ማህበረሰቦች የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታወቀ። ባለፈው መጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ ቦይንግ 737 ማክስ 8 ከአዲስ አበባ ወደ ናይሮቢ በመብረር ላይ እያለ ባጋጠመው የመከስከስ አደጋ የ157 ሰዎች ህይወት ማለፉ ይታወሳል። በሌላ በኩል ንብረትነቱ የኢንዶኔዥያው ላየን ኤይር የሆነው ተመሳሳዩ 737 ማክስ 8 አውሮፕላን በተነሳ በጥቅት ደቂቃ ውስጥ በጃካርታ ባህር ዳርቻ ተከስክሶ የ189 ሰዎች ህይወት መጥፋቱም የሚታወስ ነው። በዚህም ኩባንያው በኢትዮጵያና ኢንዶኔዥያ አየር መንገዶች ላይ በደረሰው አደጋ ሳቢያ በርካታ ክሶች በተጎጂዎች ቀርበውበት ነበር። ይሁንና አሁን ላይ የሚያደርገው የ100 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ በቀረቡበት ክሶች ሊከፍል የሚገደደውን ካሳ የሚጨምር እንዳልሆነ ተጠቁሟል። ቦይንግ የሚሰጠው ይህ የገንዘብ ድጋፍ በደረሰው ጉዳት ተጎጂ ለሆኑ ቤተሰቦችና የህብረተሰብ ክፍሎች ትምህርትን ጨምሮ የተለያዩ ለኑሮ የሚያስፈልጉ ወጪዎች የሚውል እንደሆነ ኩባንያው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። እነዚህ የድጋፍና ማህበረሰባዊ ልማት መርሃ ግብሮች የሚከናወኑት ከተለያዩ መንግስታዊ ካልሆኑ የእርዳታ ድርጅቶች ጋር በመተባበር መሆኑንም ኩባንያው ጠቅሷል። "ቦይንግ ኩባንያ በተፈጠረው አደጋ ህይወታቸውን ላጡ የተሰማው ሀዘን ጥልቅ ነው ፤ ይህ ለመጀመረፊያ ጊዜ የተበረከተው የገንዘብ ድጋፍ ተጎጂ ቤተሰቦችን ለማፅናናት ያግዛል የሚል ተስፋ አለን፤" ሲሉ የኩባንያው ሊቀመንበርና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዳኒስ ሙሌነበርግ ተናግረዋል። ምንም እንኳን ኩባንያው የገንዘብ ድጋፉን ቢያደርግም የተጎጂ ቤተሶቦች ጠበቆች ግን 'የገንዘብ ድጋፉ የተጎጂ ቤተሰቦችን አይክስም' በማለት ተቃውሟቸውን እያቀረቡ እንደሚገኙ ቢቢሲ ዘግቧል። በርካታ የተጎጂ ቤተሶቦች የገንዘብ ካሳ ሳይሆን ከአደጋው በስተጀርባ ያለውን እውነታ እንደሚሹም ነው ዘገባው ያመለከተው። በመሆኑም እንደነዚህ አይነት ችግሮች ሲከሰቱ ኩባንያው በፍጥነት ምላሽ መስጠት እንዳለበትም ጠበቆቹ ተናግረዋል። የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች እስከ አሁን ድረስ ከማንኛውም በረራ እንደታገዱ ናቸ። በኢትዮጵያ አየር መንገድና በኢንዶኔዥያ ላየን ኤይር ላይ የደረሰው አደጋ መነሻ የሶፍትዌር ችግር ከሆነ ኩባንያው ለእያንዳንዱ ሟች ቤተሶቦች 1 ሚሊዮን ዶላር ካሳ መክፈል እንደሚጠበቅበት አለም አቀፍ ተንተኞች እየተናገሩ ይገኛሉ።