የገቢዎች ሚኒስቴር በኤሌክትሮኒክስ የተደገፈ የግብር አከፋፈል ስርዓትን ገቢራዊ አደረገ

ሰኔ 27/2011 በኢትዮጵያ ገቢዎች ሚኒስቴርና ተጠሪው ጉምሩክ ኮሚሽን ውስጥ በኤሌክትሮኒክስ የተደገፈ ዘመናዊ አሰራር ስርዓት መዘርጋቱ ቀልጣፋ አገልግሎትን እየፈጠረ መሆኑን ግብር ከፋዮች ገለፁ። በገቢዎች ሚኒስቴር ለሥራ አመቺ የሆነ ስርዓት ለመፍጠር በተከናወኑ ተግባራት  ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ ላይ በኢትዮጵያ ለሥራ አመቺ የሆነ ስርዓት ለመዘርጋት በተለያዩ ተቋማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸው ተወስቷል። በዚህ ረገድ ከተከናወኑት ተግባራት አንዱ የንግዱ ማህበረሰብ የ16 የመንግስት ተቋማትን አገልግሎት በአንድ ማዕከል ማግኘት ይችል ዘንድ  የተዘረጋው አሰራር ስርዓት እና ክፍያዎች በኤሌክትሮኒክስ መፈፀም መጀመሩ ተጠቅሷል። ከእነዚህ ተቋማት መካከልም የገቢዎች ሚኒስቴርና ተጠሪነቱ ለሚኒስቴሩ የሆነው የጉምሩክ ኮሚሽን እንደሚገኙበት ተመልክቷል። በዚህም ዘመናዊ አሰራር ለመዘርጋት እንዲቻል የ6 ሺህ ንግዱ ማህበረሰብ ሰነዶች በኤሌክትሮኒክስ እንዲደራጁ፣ ከ5ሺህ በላይ የሚሆኑ ግብር ከፋዮች በሰነድ  አደረጃጀት ክህሎት ስልጠና እንዲያገኙ መደረጉን የገቢዎች ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ገልፀዋል። ሰነዳቸው በኤሌክትሮኒክስ ቴክኖሎጂ እንዲደራጅ ከተደረጉት መካከልም 60 ከፍተኛ ግብር ከፋዮች በኤሌክትሮኒክስ አሰራር ግብር መክፈል ጀምረዋል። በኤሌክትሮኒክስ ዘመናዊ የአሰራር ስርዓት አማካኝነት እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ጥራትና ፍጥነትን ለማምጣት እያስቻለ መሆኑን የገለፁት ግብር ከፋዮቹ  ቀደም ሲል በወጪና ገቢ ንግድ የተሰማሩ አካላት ይጠየቁ የነበሩ ሰነዶችን በ40 በመቶ መቀነስ መቻሉንም ለአብነት ጠቅሰዋል። በተጨማሪም እቃዎች ከወደብ ወደማራገፊያ ቦታ ከመድረሳቸው በፊት የተጀመረው የቅድመ ሰነድ ዝግጅት ጊዜን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል በመሆኑ የገቢ እቃዎች ሳይዘገዩ ለሚፈለገው አገልግሎት እንዲውሉ እያደረገ መሆኑንም አንስተዋል። ከናምፓክ ፓኬጂንግ ኩባያ የመጡት ወይዘሮ ቅድስት ያሚ ስራዎች በኤሌክትሮኒክስ ተደግፈው መከወናቸው ጊዜን የሚቆጥብ እንደሆነ ተናግረዋል። የአንድ መስኮት አገልግሎት መሰጠቱም በአንድ ቦታ የበርካታ ቢሮዎችን ግልጋሎት ማግኘት እንዲችሉና በዘርፉ የሚኖረውን ህገወጥ አሰራር ለመፍታት የሚያግዝ መሆኑን ያብራራሉ። አሰራሮቹ ስራን የሚያቀላጥፉና ውጤታማነትን የሚያሳድጉ መሆናቸውን ገልፀው ስራው በመስሪያቤቶቹ ሁሉም ቅርንጫፎች ተግባራዊ መሆን አለበት ያሉት ደግሞ የዩሮ ኬብል ንግድ ድርጅቱ አቶ ሰዓድ ኢብራሂም ናቸው። የገቢዎች ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ሚኒስቴሩ ለንግዱ ማህበረሰብ ቀልጣፋና አመቺ አገልግሎት ለመፍጠር የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ እቅዶችን ይዞ እየሰራ መሆኑን  ገልጸዋል። የካሽ ሬጅስተር ማሽን ለማግኘት ይፈጅ የነበረውን የሰባት ቀን ወደሶስት ቀን ዝቅ ለማድረግ በሙከራ ደረጃ መጀመሩን የተናገሩት ሚኒስትሯ ይህም  ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል። በሙከራ ደረጃ የተጀመረው የአንድ መስኮት አገልግሎት በቀጣይ ዓመት ወደሙሉ ትግበራ እንደሚገባ በመጠቆም። ስራዎችን ለማዘመንና የተቀላጠፈ ግልጋሎት ለመስጠት የተጀመረው ስራ ኢንቨስትመንትን የሚያስፋፋና ስራ አጥነትን ለመቀነስ የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል። አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን ከመላመድ አኳያ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ግብር ከፋዩንና ሰብሳቢውን የማለማመድና የማሰልጠን ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላልም ብለዋል። አገልግሎቱን ምቹና ተደራሽ እንዲሁም ቀልጣፋ ለማድረግ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሰራቱንና በታክስ ንቅናቄው ከግብር ከፋዩም ጋር በመወያየት ችግሮችን ለመፍታት መቻሉንም አብራርተዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በ2010 ዓ.ም 230 ቢሊዮን ብር ገቢ ለማሰባሰብ ታቅዶ 176 ቢሊዮን ብር ነበር መሰብሰብ የተቻለው። ዘንድሮ በተካሄደው የታክስ ንቅናቄና ተግባራዊ በሆኑት ዘመናዊ አሰራሮች ሳቢያ እየተጠናቀቀ ባለው የ2011 በጀት ዓመት 11 ወራት ብቻ 178 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ተሰብስቧል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም