ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅን ለዝርዝር እይታ ለቋሚ ኮሚቴ መራ - ኢዜአ አማርኛ
ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅን ለዝርዝር እይታ ለቋሚ ኮሚቴ መራ
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2011/ኢዜአ/የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅን ለዝርዝር እይታ ለህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መራ። ምክር ቤቱ ባካሄደው 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 47 መደበኛና 9ኛ ልዩ ስብሰባው የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ረቂቅ አዋጅን ለዝርዝር እይታ ወደ ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል። በረቂቅ አዋጁም የተደረጉ ዋና ዋና ማሻሻያዎች መካካል በክልል ምክር ቤት ውሳኔ መሰረት የሚደረግ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ምርጫ ከጠቅላላ ምርጫ ጋር እንዲካተት የሚል ይገኝበታል። የምርጫ ክልሎች የሚካለሉበትና በአወሳሰኑ ላይ ሊነሱ የሚችሉ ክርክሮች የሚፈቱበትን አካሄድ በግልጽ ማስቀመጥ። የምርጫ ጣቢያና የምርጫ ክልል ምርጫ አስፈጻሚና አቤቱታ ሰሚ ኮሚቴዎች አባላት የሚሰየሙበትና የሚመረጡበትን ሁኔታ ነጻነት ፣ ገለልተኛነት፣ ብቃትን፣ አሳታፊነትንና ጾታና እኩልነትን መሰረት ያደረገ እንዲሆኑ ማስቻል ጥቂቶቹ ናቸው። በተጨማሪ ቋሚ የመራጮች ምዝገባ እንዲኖርና ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ለምርጫ መጠቀም የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ እንዲኖር መሰረት ማስቀመጥ የሚሉ ዋና ዋናዎቹ ማሻሻያዎች ናቸው። የምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት የኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱ በአገሪቷ የሚካሄደው ምርጫ ግልጽ፣ ተአማኒና ፍትሃዊ እንዲሆን ያግዛል። ቀደም ሲል በአገሪቱ የኢትዮጵያ የምርጫ ህግ አዋጅ ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምዝገባ አዋጅና የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ ስነ-ምግባር ለመደንገግ የወጡ አዋጆች መኖራቸውንም አስታውሰዋል። አባላቱም አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ወደ ህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲመራም ቋሚ ኮሚቴው ረቂቁን በትኩረት እንዲያየው አሳስበዋል። አዋጁ ከዚህ ቀደም በነበረው የአገሪቷ የምርጫ ሂደት በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያስነሱ የነበሩ ችግሮችን ሊመልስ በሚችል መልኩ መቃኘት እንዳለበትም እንዲሁ። በተለይ ስለ ወሰንና የህዝብ ብዛት፣ የምርጫ ቦርድን መስፈርት የማያሟሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተመለከተና በምርጫ ህጉ ‘’የቅይጥና ትይዩ’’ የምርጫ አሸናፊ ያልፋል የሚለው በዝርዝር ሊታይ ይገባል ብለዋል። ከምክር ቤቱ አባላት አንዳንዶቹ ይህን ሰፊ ይዘት ያለው አዋጅ በአጭር ጊዜ ውስጥ አይቶ አስተያየት ለመስጠትና ለመመርመር የተሰጠው ጊዜ አነስተኛ ነው ብለዋል። ሊጠናቀቅ ጥቂት ቀናት በቀሩት የበጀት ዓመት የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማቋቋሚያ አዋጅ መጽደቁ ይታወሳል።