ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የቱሪስት መስህቦችን በማስጎብኘት ተጠቃሚ መሆን አልተቻለም--ምሁራን

ጋምቤላ ሰኔ 27 ቀን 2011 በጋምቤላ ክልል በቂ የመሠረተ ልማት አውታሮች ባለመዘርጋታቸው የቱሪስት መስህቦችን በማስጎብኘት ተጠቃሚ መሆን እንዳልተቻለ ተጠቆመ፡፡ የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ በክልሉ የቱሪስት መዳረሻዎችና ባሉባቸው ተግዳሮቶች ዙሪያ ከዘርፉ ባለሙያዎች ጋር ተወያይቷል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የዱር እንስሳትና ኢኮ-ቱሪዝም ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህር ሰለሞን ቶማስ እንደገለጹት በክልሉ ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ ባህላዊ ፣ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ መስህቦች ቢኖሩም ፤ የመሠረተ ልማት አውታሮች ባለመዘርጋታቸው ዘርፉ ማደግ አልቻለም፡፡ በክልሉ በተለይም የመንገዶችና የትራንስፖርት አገልግሎት አለመሟላት ፣የሆቴሎች አለመስፋፋትና መስህቦቹን የማስተዋወቅ ሥራ ደካማነት እንዲሁም የሰለጠነ የሰው ኃይል እጦት ዋነኛ ተግዳሮቶች መሆናቸውን አስቀምጠዋል፡፡ በዚህም ዘርፉ የሚጠበቅበትን ያህል ለክልሉ ልማት አስተዋጽኦ እንዳላበረከተ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ዘርፉን ለማሳደግ  ወጣቶችን ያሳተፈ እንቅስቃሴ በማድረግ መንግሥትና የሚመለከታቸው አካላት ቅንጅታዊ ሥራ መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የባህል፣ታሪክና ቅርስ ልማት ዳይሬክተር አቶ ኡገቱ አዲው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በክልሉ ለቱሪስት መስህብነት የሚያገለግሉ የአለባበስ፡የደስታና የኅዘን መግለጫዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይም በክልሉ የሚገኘው ብሔራዊ ፓርክ በውስጡ ብዝኃ ሕይወትን ቢኖሩትም፤ የማስተዋወቅና የመንገድ ችግሮች ስላሉበት የጎብኚዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክ የዱር እንስሳት ቱሪዝም ባለሙያ ወይዘሮ ሚሚቱ አበበ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት በፓርኩ ያለው የእንስሳትና አዕዋፍ ፍሰት በተሻለ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ በተለይም በፓርኩ ላይ ችግር ሲያስከትሉ የነበሩ የፈላታ አርብቶ አደሮች አካባቢውን ለቀው በመሄዳቸው የዱር እንስሳቱ እየተመለሱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ጎብኚዎች ቁጥር ለመጨመር ባለድርሻ አካላት ተቀናጅቶ መሥራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ በክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የቱሪዝም ልማት ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ አይችሉም አይደፈር የጎብኚዎችን ቁጥርና ገቢውን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በዚህም  ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ለማስተዋወቅና የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት  ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በቀጣይም የመሠረተ ልማት አውታሮችን ለማሟላት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡ ክልሉ በዚህ ዓመት 12ሺህ ቱሪስቶችን በማስተናገድ ሦስት ሚሊዮን ብር ለማስገባት እንዳቀደ ለማወቅ ተችሏል። በክልሉ የጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክን ጨምሮ ባህላዊ እሴቶች፣መካነ መቃብሮች፣ ሐይቆች፣የሐይማኖት ተቋማትን  የሚያካትቱ ሰው ሰራሽና ተፈጥሮአዊ መስህቦች እንደሚገኙ የቢሮው መረጃ ያሳያል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም