በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሰራተኞች ፍልሰት እየተባባሰ መጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሰራተኞች ፍልሰት እየተባባሰ መጥቷል
ሰኔ 27/2011 በኢንዱስትሪ ፓርኮች ሰራተኞች የሚከፈላቸው ደሞዝ ዝቅተኛ በመሆኑ ከስራ የሚለቁት ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱ ተገለጸ። በበጀት ዓመቱ በመንግስት ከሚለሙ ሰባት ኢንዱስትሪ ፓርኮች 110 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱም ተገልጾል በ2011 በጀት ዓመት ብቻ ከ27 ሺህ በላይ ሰራተኞች ይሰሩበት ከነበረው የኢንዱስትሪ ፓርክ መልቀቃቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ሰራተኞቹ ከስራ ገበታቸው የሚለቁበት ምክንያትም የሚከፈላቸው ደሞዝ ዝቅተኛ በመሆኑ የቤት ክራይን ጨምሮ ሌሎች ወጪዎችን መሸፈን ባለመቻሉ መሆኑ ታውቋል። የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ሌሊሴ ነሜ ለኢዜአ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ በሰባት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ብቻ ከ90 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል። በእነዚህ ፓርኮች ለ50 ሺህ በቋሚነትና ለ39 ሺህ ዜጎች ደግሞ በጊዜያዊነት የስራ እድል ተፈጥሯል። ሆኖም በተያዘው ዓመት ብቻ ከ27 ሺህ በላይ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሰራተኞች የሚከፈላቸው ደሞዝ ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በመኖሪያ ቤትና ሌሎችም ተያያዥ ችግሮች ስራቸውን ማቆማቸውን ገልጸዋል። ፓርኮቹ ከሰራተኞች መኖሪያ አካባቢ ርቀው ስለሚገኙ ለተጨማሪ ወጭ እየዳረጓቸው ሲሆን ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተዳምሮ በስራቸው ላይ እንደይዘልቁ አስገድዷቸዋል ነው ያሉት። ''ኮርፖሬሽኑ ፓርኮችን የመገንባትና መሰረተ ልማቶችን ከማሟላት አልፎ የሰራተኞችን መኖሪያ ለመገንባት በጀት የለውም'' ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ባለሃብቱ ራሱ ቤቱን እንዲገነባ የሚያስችል ሁኔታን ማመቻቸቱን አብራርተዋል። ለአብነትም ቦሌ ለሚ ቁጥር አንድ ኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ አንድ ባለሃብት ለ4 ሺህ ሰራተኞች መኖሪያ ቤት ገንብተው በማጠናቀቃቸውን ጠቅሰዋል። በሌሎች ፓርኮችም ባለሃብቶች ፍላጎት እያሳዩ በመሆኑ መሬት እንዲሰጣቸውና የግንባታ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነጻ የሚያገኙበት ዕድል መመቻቸቱን አመልክተዋል። በሌላ በኩል ከሁለት ቀናት በኋላ በሚጠናቀቀው በጀት ዓመት በመንግስት ከሚለሙ ሰባት ኢንዱስትሪ ፓርኮች 110 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱ ነው የተገለጸው። አዳማ፣ መቀሌና ድረዳዋ ላይ ያጋጠመው የውሃ እጥረት፣ ወደ ስራ ለመግባት ዝግጁ በሆኑ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ላይ የሃይል አቅርቦት እንዲሁም የቤት ችግር በበጀት ዓመቱ ካጋጠሙ ዋና ዋና ተግዳሮቶች ናቸው ብለዋል። በተያዘው በጀት ዓመት አዳማ፣ ጅማና ደብረ ብርሃን ኢንዱስትሪ ፓርኮች ተመርቀው ወደ ስራ የገቡ ሲሆን ቦሌ ለሚ ምዕራፍ ሁለት፣ ቅሊንጦ ድሬዳዋና ባህር ዳር ኢንዱስትሪ ፓርኮችም ግንባታቸው ተጠናቆ ለስራ ዝግጁ መሆናቸውን ወይዘሪት ሌሊሴ ገልጸዋል። የኮርፖሬሽኑ ሰራተኞችና ባለድርሻ አካላት በዛሬው እለት በቦሌ ለሚ ኢንዱስትሪ ፓርክ የ2011 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸማቸውን ገምግመዋል።