ቀጥታ፡

ኢንቨስትመንት ረቂቅ አዋጁ የስራ ዕድል ፈጠራን፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን፣ የዕውቀትና ቴክኖሊጂ ሽግግርን ለማጠናከር ያስችላል

ሰኔ 27/2011 የተሻሻለው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ረቂቅ አዋጅ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ የስራ ዕድል ፈጠራን፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን፣ የዕውቀትና ቴክኖሊጂ ሽግግርን ለማጠናከር በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ መሆኑን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ። ረቂቅ አዋጁ በመጪው ዓመት የመጀመሪያው ሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃልም። ኮሚሽኑ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በረቂቅ አዋጁ ላይ ያዘጋጀው የውይይት መድረክ ዛሬ ተጀምሯል። የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ አበባየሁ በዚህ ወቅት እንዳሉት ላለፉት ስድስት ዓመታት ስራ ላይ የነበረው የኢንቨትመንት አዋጅን ለማሻሻል ላለፉት አራት ወራት ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ሲሰራ ቆይቷል። የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ፍሰት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያደገ ቢመጣም አገሪቱ ካላት እምቅ ምጣኔ ኃብታዊ አቅም አንጻር በቂ አይደለም ብለዋል። በመሆኑም አዲስ መዋእለ ንዋይ፣ እውቀትና ቴክኖሎጂ በመሳብ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ዒላማ ያደረጋቸውን የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የውጭ ምንዛሬና ዕውቀትና ቴክኖሊጂ ሽግግር ዕውን ለማድረግ አዋጁን ማሻሻል አስፈልጓል ነው ያሉት። ተወዳዳሪ ኢንቨስትመንት ለመሳብ የዓለም አቀፉን ተለዋዋጭ ኢኮኖሚ ግምት ውስጥ ያስገባ የህግ ማዕቀፍ መተግበር ያስፈልጋል ያሉት ኮሚሽነሩ፣ አዲስ የሚሻሻለው አዋጅ ዘመናዊ፣ ተገማችና ግልጽነት ያለው ኢንቨስትመንት ፍሰት ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል። የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደግል ለማዞር በተጀመረው ጥረትም ከዚህ በፊት ለግል ዘርፍ ዝግ የነበሩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለግሉ ዘርፍ ክፍት ማድረግም ሌላው የአዋጁ ማሻሻያ ዓላማ ነው። ከዚህም በተጨማሪ አዋጁ የኢንቨስትመንት አስተዳድር ስርዓት ለመዘርጋት፣ በፌዴራልና ክልል ባለድርሻ አካላት መካከል የተሻለ ቅንጅታዊ አሰራር ለመዘርጋትና ለተለዩ የኢኮኖሚ መስኮች ልዩ ማበረታቻዎች በሚሉ ጉዳዮች ላይ አዳዲስ ድንጋጌዎች እንደተካተቱበት ተመልክቷል። ረቂቅ አዋጁ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨሰትመንት ብቻ ሳይሆን በአገር በቀል ባለሀብቶች ከውጭ ባለሀብቶች ጋር በቅንጅት የሚሰሩበት አሰራር እንዲፈጠር ያስችላልም ተብሏል። ረቂቅ አዋጁ በቀጣይ በሚደረጉ የውይይት መድረኮች አስፈላጊ ግብዓቶች ተካተውበት በ2012 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ይጸድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም