ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ዝላይንና ውርወራን ለመሳሰሉ የሜዳ ላይ ስፖርታዊ ውድድሮች ትኩረት አለመሰጠቱ ተገለጸ

አዲስ አበባ ሰኔ 3/2010 በኢትዮጵያ ዝላይንና ውርወራን ጨምሮ በአትሌቲክስ ውስጥ ለሚካተቱት የሜዳ ላይ ስፖርታዊ ውድድሮች ትኩረት አልተሰጠም ሲሉ አትሌቶች ተናገሩ። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በበኩሉ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችሉ ጥረቶችን መጀመሩን አስታውቋል። የከፍታ፣ የእርዝመትና የምርኩዝ ዝላዮች  እንዲሁም የአሎሎ፣ ዲስክ፣ የመዶሻና ጦር ውርወራዎች ትኩረት እንዳልተሰጣቸው በየዘርፎቹ የሚወዳደሩ አትሌቶች ተናግረዋል፡፡ የአዳማ ከተማ አትሌቲክስ ክለብ የምርኩዝ ዝላይ ስፖርት ተወዳዳሪው አብዲሳ በዳሶ እንዳለው ውድድር ሲኖር ከማወዳደር ባለፈ ከውድድር በፊት ተገቢውን ስልጠና በመስጠት ረገድ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ የመከላከያ አትሌቲክስ ስፖርት ክለብ የርዝመትና የምርኩዝ ዝላይ ተወዳዳሪ አትሌት አዲር ጉር በበኩሉ ትኩረት በተነፈገው በሜዳ ላይ አትሌቲክስ ስፖርት ውድድር ውጤታማ ለመሆን የአሰልጣኞችን ደረጃ  ማሻሻል የሚያስችሉ ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው ተናግሯል። የሲዳማ ቡናው የከፍታ ዝላይ ተወዳዳሪ  አትሌት ዲፔ ሌም በሰጠው አስተያየት ደግሞ ኢትዮጵያውያን በተክለ ቁመናም ሆነ በጉልበት ረገድ ለእነዚህ ስፖርታዊ ውድድሮች የተመቹ ቢሆኑም  ዘርፉ ትኩረት በማጣቱ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ መወዳደር አንዳልቻለች ገልጿል። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተር አቶ ዱቤ ጅሎ በሰጡት ምላሽ "በሀገሪቱ የሜዳ ላይ ስፖርታዊ ተግባራት አንዲያድግ አስካሁን የተከናወነ ይህ ነው የሚባል መልካም ተግባር የለም፤ ፌዴሬሽኑም  የሚጠበቅበትን ባለመወጣቱ በክልሎችም በውርወራና ዝላይ ስፖርቶች ያለው እንቅስቃሴ ደካማ ነው" ብለዋል። ሆኖም በመጪዎቹ ጊዜያት በዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ጥረቶች መጀመራቸውን ገልፀዋል። ፌዴሬሽኑ ከዓለም አቀፉ ስፖርት  ማህበር ጋር በመነጋገር በዝላይ፣ ውርወራና  መሰል ስፖርታዊ ውድድሮች ስልጠና የሚሰጡ ባለሙያዎችን በአገር ውስጥ ማግኘት እንዳልተቻለም ነው የተናገሩት። በዚህም ስልጠናውን  ከውጭ በሚጋበዙ ሙያተኞች ለመስጠት የሚያስችሉ ስራዎች መጀመራቸውን  አቶ ዱቤ አስታውቀዋል። ከወራት በፊት ከጋናና ናይጄሪያ ባለሙያዎችን ለማስመጣት የተደረገው ጥረት ከክፍያና ከጉዞ ሰነድ  ጋር በተያያዘ በተፈጠረ አለመግባባት ሳይሳካ መቅረቱን ገልጸው፣ ባለሙያዎችን ከውጭ ሀገራት የማፈላለጉ ጥረት መቀጠሉን አስታውቀዋል። የኢትዮጵያና ቻይና አትሌቲክስ ማህበራት በዘርፉ ልምድ መለዋወጥ የሚያስችላቸውን የትብብር ስምምነት ከሶስት ወር በፊት መፈራረማቸው ይታወሳል። በስምምነቱ መሰረትም ቻይና በአጭር ርቀት ውድድሮች ለኢትዮጵያ ልምድ የምታካፍል ሲሆን ኢትዮጵያ በበኩሏ በዓለም ውጤታማ በሆነችበት በመካከለኛና ረጅም ረቀት ያላትን ልምድ ለቻይና ታካፍላለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም