ቀጥታ፡

ትናንት በሐረር የገበያ ሥፍራ በተከሰተ የእሳት ቃጠሎና የንብረት ዝርፊያ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ሰኔ 26/2011 (ኢዜአ) በሐረር ከተማ ሸዋበር መብራት ኃይል በተባለ የገበያ ሥፍራ ትናንት በተከሰተ የእሳት ቃጠሎና የንብረት ዝርፊያ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ጣሰው ቻለው ለኢዜአ እንደገለጹት በገበያ ስፍራው የደረሰውን የእሳት አደጋ ለማጣራት ኮሚቴ ተዋቅሮ  ከትላንት ጀምሮ እንቅስቃሴ ጀምሯል። በዚህም በእሳት ቃጠሎውና በንብረት ዘረፋ የተጠረጠሩ ስድስት ግለሰቦች በቁጥጥር  ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አመልክተዋል። ተጠርጥረው ከተያዙት ግለሰቦች መካከል 3ቱ ተከስቶ በነበረው የእሳት ቃጠሎ አደጋ የተጠረጠሩ ሲሆን ቀሪዎች የተያዙት ንብረት ዘርፈዋል በሚል ነው። እንደ ኮማንደር ጣሰው ገለጻ በአሁኑ ወቅት የገበያ ስፍራው የተረጋጋ ሲሆን ህብረተሰቡም የተበታተኑ እቃዎችን ከፖሊስ ጋር በመሆን የማሰባሰብ ሥራ እያከናወነ ይገኛል። በገበያ ማዕከሉ የወደሙ ንብረቶችን በአግባቡ ለመለየት በእሳት አደጋው ተጎጂ የሆኑ ነጋዴዎች የተወከሉበት ኮሚቴ በማዋቀር ንብረት የማረጋገጥና መሰል ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቡድን የአደጋውን መንስኤ ለማረጋገጥ ከፌዴራል ፖሊስ የእሳት ቃጠሎ ሙያተኛ በማስመጣት ከዛሬ ጀምሮ የተጠናከረ የምርመራ ሥራ ማከናወን መጀመሩንም ገልጸዋል። በሐረር ከተማ በተለምዶ መብራት ኃይል በተባለው የገበያ ሥፍራ ትላንት ተከስቶ በነበረው የእሳት አደጋ 307 ሱቆች መቃጠላቸውን ኮማንደር ጣሰው አያይዘው ገልጸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም