የቱሪዝም መለያ ስም ከማስተዋወቅ ባሻገር ለመስህቦች ጥበቃ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የቱሪዝም መለያ ስም ከማስተዋወቅ ባሻገር ለመስህቦች ጥበቃ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል
ሰኔ 26 / 2011 የኢትዮጵያን የቱሪዝም መለያ ስም ከማስተዋወቅ ባሻገር የቱሪዝም መስህቦች እንክብካቤና ጥበቃ ስራው ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባው የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ። ቱሪዝም ኢትዮያና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በጋራ በመሆን "ምድረ ቀደምት" በሚለው የኢትዮጵያ የቱሪዝም መለያ ስም ላይ ያዘጋጁት የማስተዋወቂያ ኮንፍረንስ ዛሬ በሐረሪ ክልል ተካሄዷል። በኮንፍረንሱ ላይ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ የሆቴል ባለቤቶች፣ የቱሪዝም ልማት መምህራንና ሌሎችም ተሳትፈውበታል። ኢትዮጵያ የሚዳደሱና የማይዳሰሱ የቱሪስት መስህቦች ባለቤት ብትሆንም አያያዝና እንክካቤ ላይ ክፍተት እንዳለባት በውይይቱ ተነስቷል። የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ውብሸት ክንፈ አዲሱን የኢትዮጵያ የቱሪዝም መለያ ስም በአዲስ መልክ ማስተዋወቁ መልካም ቢሆንም "በቱሪስት መስህቦቹ ላይ በቂ ጥበቃ ካልተደረገ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት ያስቸግራል" ብለዋል። በአሁኑ ወቅት በአገሪቷ ያሉ የቱሪስት መስህቦች ከትኩረት ማነስ የተነሳ አደጋ ላይ ሲወድቁ እንደሚስተዋልም አክለዋል። ስለዚህም የማስተዋወቁ ስራ ውጤታማ እንዲሆን ቅርሶች ጥንታዊነታቸውን ጠብቀው እንዲታደሱና ያሉትም ጉዳት እንዳይደርስባቸው ሁሉም አካላት ትኩረት ሰጥተው መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል። ኢትዮጵያ ከሚዳሰሱ ቅርሶቿ ባሻገር ከባህላዊ አኗኗር የክብረ በዓላት አከባበርና መሰል ክንውኖች ጋር የተያያዙ ቅርሶቿን በባህል ወረራ ምክንያት እያጣች እንደሆነ የገለጹት ደግሞ ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ሰለሞን ገብረእግዝጊ ናቸው። በመሆኑም እነዚህን ባህሎች በመጠበቅ ጎብኚዎች ስለ ኢትዮጵያ ያላቸውን አስተሳሰብ ማሳደግና አዲሱን የኢትዮጵያ የቱሪዝም መለያ ስም በራሳቸው እንዲያስተዋውቁ መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል። ሌላኛው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ሃይለጊዮርጊስ መገርሳ በበኩላቸው የቅርሶችን ደህንነት ለመጠበቅ የአካባቢውን ህብረተሰብ ከሀብቶቹ ተጠቃሚ ማድረግ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም የከተማ ጽዳትና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበትም ገልጸዋል። በቱሪዝም ኢትዮጵያ የገበያ ቡድን መሪ አቶ ወልደገብርኤል በርሄ በበኩላቸው የኢትዮጵያን የቱሪዝም አቅም ለዓለም ከማስተዋወቅና ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የቱሪስት መስህቦችን ደህንነት ከማረጋገጥ አኳያ ተቋሙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። የአካባቢውን ማህበረሰብ በቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች የዕደ ጥበብ ውጤቶችን መሸጥና ከተጓዳኝ ስራዎች ተጠቃሚ እንዲሆን ከተለያዩ ተቋማት ጋር እየሰራን ነውም ብለዋል። "ምድረ ቀደምት" የሚለውን የቱሪዝም መለያ ስም የማስተዋወቅ ስራ በመገናኛ ብዙሃን፣ በህትመት እና በተለያዩ የቴክኖሎጂ አውታሮች ለዓለም የማድረስ ስራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። በአገር ውስጥም በሁሉም ክልሎች የቱሪዝም መለያ ስሙን ለማህበረሰቡ የማስተዋወቅ ስራ እንደሚቀጥልም አክለዋል። አራተኛው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤት ስብሰባ በመጋቢት ወር 2009 ባካሄደው ዓ.ም "የ13 ወር ጸጋ" የሚለው የቱሪዝም መለያ ወደ "ምድረ ቀደምት" ወይም (Land of Origins) ተቀይሮ በይፋ መመረቁ የሚታወስ ነው።