ቀጥታ፡

የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አፈፃፀም ከ67 በመቶ በላይ መድረሱ ተገለጸ

ሰኔ 26/2011 ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ አፈፃፀም 67 ነጥብ 9 በመቶ መከናወኑን የግድቡ ህዝባዊ ተሳትፎ ብሔራዊ አስተባባሪ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ፅህፈት ቤቱ ለአገር ውስጥ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የግድቡን የግንባታ ክንውን እያስጎበኘ ነው። የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ኤፍሬም ወልደ ኪዳን ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እንደተናገሩት የግድቡ ግንባታ ቀደም ሲል አጋጥሞት የነበረውን ችግር ሙሉ በሙሉ ተወግዶ ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል። የዋናው ግድብ ግንባታ 80 በመቶ፣ የግድቡ የቀኝ ኃይል ማመንጫ ቤት ግንባታ 63 በመቶ፣ የግራ ኃይል ማመንጫ ቤት ግንባታ ደግሞ 74 በመቶ ደርሷል። የግድቡ የጎርፍ ማስተንፈሻ ግንባታ 96 በመቶ፣ የኮርቻ ግድቡ ግንባታ 95 በመቶና የኃይል ማስተላለፊያ መሣሪያ ማረፊያ ሥፍራም 66 በመቶ መከናወኑን አብራርተዋል። በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ አፈጻጸም በአማካይ 67 ነጥብ 9 መድረሱን ኢንጂነር ኤፍሬም ተናግረዋል። ግድቡ በ2013 ዓ.ም የመጀመሪያ ምዕራፍ ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምር ይጠበቃል ያሉት  ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጁ በ2015 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ደግሞ ግንባታው ተጠናቆ በሙሉ አቅሙ ኃይል ማመንጨት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም