አፍሪካ በቡና ማምረት ከፍተኛ አቅም ያላት አህጉር ብትሆንም እየተጠቀመችበት አይደለም - ኢዜአ አማርኛ
አፍሪካ በቡና ማምረት ከፍተኛ አቅም ያላት አህጉር ብትሆንም እየተጠቀመችበት አይደለም
ሰኔ 26 / 2011 አፍሪካ በቡና ማምረት ረገድ ከፍተኛ አቅም ያላት አህጉር ብትሆንም በአግባቡ እየተጠቀመችበት እንዳልሆነ ተገለጸ። የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን በአፍሪካ የቡና ፍጆታን ማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት ጋር መክሯል። ምክክሩ በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ያሉ አገራት ለተለያዩ የውጭ አገራት ከሚልኳቸው ቡና ባሻገር ምርቱን በአገር ውስጥ በመጠቀም የሚገኘውን ገቢ ማሳደግ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጓል። የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አዱኛ ደበላ እንደገለጹት፤ አፍሪካ በቡና ማምረት ረገድ ከፍተኛ አቅም ያላት አህጉር ናት። ኢትዮጵያም ቡናን በከፍተኛ ደረጃ ከሚያመርቱ አገራት መካከል ተጠቃሽ ስትሆን 50 በመቶ ያህል ቡናን በአገር ውሰጥ ትጠቀማለች። ኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛንያ፣ ዝምባቡዌ፣ ሩዋንዳ፣ደቡብ ሱዳንና ናይጄሪያ ደግሞ ቡናን በተሻለ ሁኔታ የሚያመርቱና የሚጠቀሙ አገራት መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይሁንና በርካታ የአፍሪካ አገራት ቡናን የማምረት አቅም ያላቸው ቢሆኑም በአገር ውስጥ በሚፈለገው መጠን የመጠቀም ሁኔታቸው ግን ዝቅተኛ መሆኑን አመልክተዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ቡናን በአገር ውስጥ የምትጠቀምበትን መንገድ ለሌሎች ቡናን የማምረት አቅም ያላቸው የአፍሪካ አገራት ይህንን እንዲከተሉ ልምድ እንደምታካፍል ገልጸዋል። በተለይም ወደ አውሮፓ፣ አሜሪካና እሲያ የሚላከውን ቡና አፍሪካ ውስጥ በመጠቀም ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን ገቢ ማሳደግ እንደሚቻል በማውሳት። ለዚህም ለውጭ አገር ከሚላከው ቡና ባሻገር በአገር ውስጥ ቡናን የመጠቀም ልምድን በማሳደግ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባም ተገልጿል። ኢትዮጵያ ወደ ውጪ በምትልከው ቡና ከአለም አቀፍ ገበያው ጋር ተወዳዳሪ እንድትሆን እሴት ጨምሮ በመላክ ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግም እየሰራች መሆኑንም ነው የገለጹት። የአገር ውስጥ የቡና ፍጆታን በመጨመርና አርሶ አደሩ የሚያመርትበት ወጪ እንዲሸፍንለት በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል። በዚህም ቡና አምራች ከሆኑ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ጋር የገበያ ሰንሰለቱን በማስፋት ከቡና የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ማሳደግ አንደሚቻልም ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ ከብራዚል፣ ቬትናም፣ ኮሎምቢያና ኢንዶኔዥያ ቀጥሎ አምስተኛዋ ቡና አምራች አገር ናት።