ድሬዳዋን የምስራቅ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል-ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለሊሴ - ኢዜአ አማርኛ
ድሬዳዋን የምስራቅ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቷል-ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለሊሴ
ድሬዳዋ ሰኔ 26 / 2011 የፌዴራል መንግሥት ድሬዳዋን የምስራቅ ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግ ትኩረት መስጠቱን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስታወቁ። ከኢትዮጵያ 12 የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል ሰባቱ ምርታቸው ወደ ውጭ መላክ ጀምረዋል፡፡ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወይዘሪት ለሊሴ ነሜ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት መንግሥት በከተማዋ እየተገነቡ የሚገኙት ፓርኮች የቀድሞው ኢንዱስትሪ ከተማነቷን ለማደስ በመሥራት ላይ ነው። በዚህም ከተማዋን የምስራቁ የአገሪቱ ክፍል የኢንዱስትሪ ከተማ ለማድረግ መሠረተ ልማት አቅርቦት ለማሟላት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ ላለፉት አራት አመታት በ3ነጥብ 98 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ፓርክ በ2012 መጀመሪያ ሥራ እንደሚጀምር ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡ ለፓርኩ ከተዘጋጀው 4 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ በመጀመሪያው ዙር ከተገነባው 150 ሄክታር መሬት ላይ የሕንድና የቻይና ባለሃብቶች ሥራ መጀመራቸውን አስረድተዋል፡ ሌሎች ባለሃብቶችን ወደ ፓርኩ ለማስገባት የተቀናጀ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ከተገነቡትና እየተገነቡ ከሚገኙት 12 የኢንዱስትሪ ፓርኮች መካከል ሰባቱ ምርታቸው ወደ ውጭ መላክ መጀመራቸውን ወይዘሪት ለሊሴ አስታውቀዋል፡፡ ፓርኮቹ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ያስገኙ ሲሆን ከ47 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ሥራ ፈጥረዋል፡፡ ቀሪዎቹ ፓርኮች ግንባታቸው ተጠናቅቆ ሥራ ሲጀምሩ ከ100 ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ሥራ እንደሚያስገኙ አስረድተዋል፡፡ ፓርኮቹ ለአገሪቱ ሥራ በመፍጠር፣ የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት፤ የቴክሎጂ ሽግግር በማምጣት አስተዋጽኦ እንዳላቸው ወይዘሪት ሌሊሴ ተናግረዋል፡፡ የድሬዳዋ ንግድ፣ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር ፓርኩ ሥራ ሲጀምር ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ሥራ ይፈጥራል ብለዋል፡፡ ከተማዋ ለጅቡቲ ወደብ ያላት ቅርበት፤ ከጅቡቲ በኮንክሪት አስፋልት መንገድ መገናኘት ፣በባቡርና አየር ትራንስፖርት መስተሳሰር የፓርኩን ተፈላጊነት እንደሚያሳድጉት አመልክተዋል፡፡ ፓርኩ ሥራ ሲጀምር የከተማዋን ማህበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ እንደሚቀይረው አቶ ከድር አስታውቀዋል፡፡ ድሬዳዋ ከ100 ዓመታት በላይ ያስቆጠረች ከተማ ስትሆን፣በምግብ፣በጨርቃ ጨርቅ፣በሲሚንቶና በሥጋ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎቿ ታዋቂነት እንደነበራት ይታወሳል።