ቀጥታ፡

ማርሴይ የአየር መንገዱ 121ኛ መዳረሻ ሆናለች

አዲስ አበባ ሰኔ 26/2011የፈረንሳይ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ የሆነችው ማርሴይ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 121ኛ መዳረሻ ሆናለች። ትናንት ከሌሊቱ 5 ሰዓት ከ45 ደቂቃ የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ፍሬድሪክ ቦንቴምስና ሌሎች ተሳፋሪዎችን ይዞ የተነሳው የኤር ባስ 780 አውሮፕላን ዛሬ ጠዋት 2 ሰዓት ከ 35 ደቂቃ ማርሴይ ከተማ ደርሷል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፈረንሳይ ከተማ ማርሴይ በረራ መጀመሩን አስመልክቶ የተዘጋጀ ስነ ስርአት ትናንት ማምሻውን ተካሄዷል። የአየር መንገዱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም የበረራው መጀመር በአፍሪካና በአውሮፓ ባሉ ከተሞች መካከል የአየር ግንኙነት እንደሚያሰፋ ተናግረዋል። አየር መንገዱ ከፓሪስ በመቀጠል ሁለተኛ የፈረንሳይ መዳረሻውን ወደ ማርሴይ ማድረጉ አዲስ አበባና ማርሴይን ከማገናኘቱ ባለፈ ማርሴይን ከተቀሩት የአየር መንገዱ የአፍሪካ ከ60 በላይ መዳረሻዎች ጋር እንደሚያገናኝም አመልክተዋል። በተጨማሪም የፈረንሳይ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ የአፍሪካ አገራትንም ከፈረንሳይ ጋር ለማገናኘትም የበረራው መጀመር የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም ገልጸዋል። የበረራው መጀመር አሁንም አውሮፓ ዋነኛ ከሚባሉት የአፍሪካ የንግድ አጋሮች መካከል አንዷ መሆኗንና ፈረንሳይም የአፍሪካ የንግድ አጋር መሆኗን ይበልጥ የሚያሳይ ነውም ብለዋል። ያለፈው አንድ ዓመት የደረሰውን አደጋ ጨምሮ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈታኝ ጊዜ እንደነበርና በአየር መንገዱ ሰራተኞች ጠንካራ ስራ ፈተናው ወደ መልካም እድል መቀየሩንም አመልክተዋል። በአቪዬሽኑ ኢንዱስትሪ አደጋ ደርሶ ቶሎ በማገገም እድገት ማስመዝገብ ብዙም ያልተለመደ ቢሆንም አየር መንገዱ ይሄንን ማሳካት መቻሉንና በአደጋው ወቅትና ከአደጋውም በኋላ ተሳፋሪዎች በአየር መንገዱ ላይ ላሳዩት እምነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። የፈረንሳይ መንግስት በየትኛውም ጊዜ አየር መንገዱ ለማስፋፋያ ሊጠቀምበት የሚችል የ120 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ማዘጋጀቱንም ጠቅሰዋል። በቀጣይም ሐምሌ 8 ቀን 2011 ዓ.ም አየር መንገዱ ከሶማሊያ ርዕሰ መዲና ሞቃዲሾ በመቀጠል በአገሪቷ ሌላኛዋ ከተማ ጋሮዌ በሳምንት ሶስት ጊዜ በረራ እንደሚጀምርም ጠቁመዋል። አየር መንገዱ አሁንም የበረራ መዳረሻዎችን የማስፋቱን ተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር ፍሬድሪክ ቦንቴምስ በበኩላቸው አየር መንገዱ በረራውን በፈረንሳይና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጎለብት እንደሆነ ተናግረዋል። የአገራቱንም የንግድ ትስስር ለማሳደግና ሁለቱ አገራት በአቪዬሽን ዘርፍ ያላቸው ግንኙነት ለማሳደግ እንደሚያግዘም ገልጸዋል። ወደ ማርሴይ የተጀመረው በረራ በከተማዋ ያሉ የአፍሪካ ዳያስፖራዎች ወደ አፍሪካ አገራት ለመጓዝ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርላቸውም አመልክተዋል። ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ አቪዬሽን አካዳሚና ለካርጎ ተርሚናል የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግዋን አስታውሰው በቀጣይም የተለያዩ ድጋፎችን ለአየር መንገዱ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነችም ገልጸዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ማርሴይ በሳምንት ሶስት ጊዜ በረራ የሚያደርግ ሲሆን ከተማዋ በአውሮፓ የአየር መንገዱ 21ኛ በዓለም አቀፍ ደረጃ 121ኛ መዳረሻው ሆናለች።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም