ቀጥታ፡

በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል የተነሳ ግጭት የህይወትና የአካል ጉዳት አስከተለ

ሰኔ 25/2011በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ በተማሪዎች መካከል በተነሳ ግጭት የህይወት፣የአካልና የንብረት ጉዳት መድረሱን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ። በዩኒቨርሲቲው በጀነራል ታደሰ ብሩ ካምፓስ ዛሬ በተነሳው ግጭት ጉዳት የደረሰባቸው ሁለት ተማሪዎች ህይወት ሲያልፍ ሌሎች አምስት ተማሪዎች መቁሰላቸው ተመልክቷል። በግቢው የተማሪዎች ዲን ዋቅጋሪ ጉልማ እንደገለጸው በህመም ላይ የነበረ አንድ ተማሪ በትላንትናው ዕለት ህይወቱ ካለፈ በኋላ በአንዳንድ ተማሪዎች ሌሊቱን ግጭት እንዲቀሰቀስ ተደርጓል። በዚህ ግጭትም ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው ሁለት ተማሪዎች ህይወት ሲያልፍ በሌሎች አምስት ተማሪዎች ላይ ቀላልና ከባድ የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም በተማሪዎች መኝታ አካባቢ ለጊዜው ግምቱ ያልታወቀ ንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከክልል ከፌዴራልና ከዞኑ የተውጣጣ ግብር-ሃይል ተቋቁሞ ተማሪዎችን ለማቀራረብና ለማግባባት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል። የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ህብረት ሊቀመንበር ዩሴፍ ደቻሳ በበኩሉ ችግሩ በተፈጥሯዊ መንገድ የሞተን ተማሪ ተገፍትሮ ነው የሞተው በሚል አንዳንድ ተማሪዎች በዩኒቨርስቲው ውስጥ በነዙት ወሬ ምክንያት መፈጠሩን ተናግሯል። በአሁኑ ወቅት በጀኔራል ታደሰ ብሩ ካምፓስ የሚገኙ ተማሪዎች ተበታትነው ያሉ ቢሆንም የማግባባት፣ በችግሩ ዙሪያ ግንዛቤ የመፍጠርና ጉዳት ያደረሱ ተማሪዎችንም በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጿል። የአንደኛ አመት የጂኦግራፊ ተማሪ አዳነ አሸናፊ በበኩሉ ምሽት ላይ ችግሩ ሊከሰት እንደሚችል አመላካች ነገሮች ሲታዩ ተገቢው ክትትል ማድረግ አስፈላጊ እንደነበረ ጠቁሟል። አሁን ላይ እሱን ጨምሮ ሌሎች ተማሪዎችም ስጋት ላይ በመሆናቸው በችግሩ ተጨማሪ ጉዳት እንዳይደርስ አስፈላጊውን ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግም ተናግሯል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም