የሐረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት በቃጠሎ ንብረታቸው የወደመባቸውን ነጋዴዎች አቋቁማለሁ አለ - ኢዜአ አማርኛ
የሐረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት በቃጠሎ ንብረታቸው የወደመባቸውን ነጋዴዎች አቋቁማለሁ አለ
ሐረር ሰኔ 25/ 2011በሐረር ከተማ በተከሰተው የእሳት ቃጠሎ ንብረታቸው የወደመባቸውን ነጋዴዎች ለማቋቋም እንደሚሰራ የከተማው ማዘጋጃ ቤት ገለጸ። የከተማው ማዘጋጃ ቤት ሹም አቶ አሪፍ መሐመድ እንደገለጹት ማዘጋጃ ቤቱ በገበያው በተከሰተው ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ ምክንያት ንብረት የወደመባቸው ነጋዴዎች በአጭር ጊዜ ወደ ቀድሞ እንቅስቃሴያቸው ለመመለስ ድጋፍ ያደርጋል። ፖሊስ የምርመራ ስራውን ጨርሶ እስኪያወጣና ማዘጋጃ ቤቱም መልሶ ግንባታውን አጠናቆ እስከሚያስረክብ ድረስ ተጎጂዎቹ ትዕግስት በተሞላበት ሁኔታ እንዲጠብቁ ጠይቀዋል። በገበያው በልብስ ስፌት ሥራ የሚተዳደሩትና አቶ ቢንሳ ብዙአየሁ በአደጋው ንብረት እንደወደመባቸው ተናግረዋል።በገበያው በተደጋጋሚ ጊዜ የሚከሰተውን እሳት ሥራቸውን ለማከናወን ችግር ፈጥሮብኛል ብለዋል። ''አደጋ ሲከሰትብኝ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። በዚህም ለበርካታ ንብረት ውድመት ተዳርጌያለሁ'' ያሉት በገበያው የተዘጋጁ አልባሳትን በመሸጥ የሚተዳደሩና በአደጋው ንብረታቸው የወደመባቸው አቶ መሐመድ አብደላ ናቸው። የእሳት አደጋ ማጥፊያ ተሽከርካሪዎች በአደጋው ሥፍራ ፈጥነው አለመድረሳቸው ቃጠሎውን በፍጥነት በቁጥጥር ሥር ለማዋል አዳጋች እንዳደረገውም ገልጸዋል። የሐረሪ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ኮማንደር ጣሰው ቻለው እሳቱን የክልሉና የፌዴራል ፖሊስና አንዲሁም የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀናጅተው ባደረጉት ርብርብ ለመቆጣጠር መቻሉን አስታውቀዋል። አደጋው ለሁለት ሰዓት ያህል ቆይቶ በቁጥጥር ሥር መዋሉንም አስረድተዋል። አደጋው ለጊዜው ግምቱ የማይታወቅ ንብረት መውደሙን የተናገሩት ኮማንደር ጣሰው፣የአደጋው መንስዔ በመጣራት ላይ መሆኑን አስረድተዋል። በሐረር ከተማ በተለምዶ ''መብራት ኃይል'' በተባለው ገበያ በ2002ና በ2007 ተመሳሳይ የእሳት አደጋ መድረሳቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።