ቀጥታ፡

''የጋምቤላ ክልል ወጣቶች አገራዊውና ክልላዊ ለውጥ በማራመድ ሚናቸውን መወጣት አለባቸው''- ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ

ጋምቤላ ሰኔ 25 / 2011 የጋምቤላ ክልል ወጣቶች አገራዊውና ክልላዊ ለውጥ በማራመድ ሚናቸውን እንዲወጡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስገነዘቡ። የጋምቤላ ከተማ ወጣቶች በክልሉ ወቅታዊ የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በውይይቱ ላይ እንዳሳሰቡት ወጣቶች በክልሉ የተጀመሩ የለውጥ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ድርሻቸውን መወጣት  አለባቸው፡፡ ወጣቶቹ በክልሉ የተጀመረውን ለውጥ እውን ለማድረግ ደጋፊ እንጂ፤ አደናቃፊ መሆን እንደሌለባቸው አመልክተዋል። ሕዝቡን ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ እንዲሁም የሕግ የበላይነትን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት ማገዝ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ ከወጣቶቹ አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት የከተማዋን ብሎም የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅ ከመንግሥት ጎን በመሆን እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡ በተለይም በክልሉ በአንድነትና በፍቅር አብረው የኖረውን ሕዝብ ለማጋጨት የሚጥሩ አካላትን በማጋለጥ ድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡ ይሁንና መንግሥትም በክልሉ የሕግ የበላይነትን በማስፈንና የሕዝቡን የልማትና መልካም አስተዳደር ችግሮችን ትኩረት ሰጥቶ እንዲመልስ ጠይቀዋል፡፡ ከተሳታፊ ወጣቶች መካከል ወጣት ቻም ኡጁሉ አብዛኛዎቹ ወጣቶች ሰላም ፈላጊና ዕውቀትን የሚሹ መሆናቸውን ገልጾ፣ወጣቱን ወደ ግጭት አስገብተው ለማትረፍ ከሚሯሯጡ አካላት ድርጊት በማክሸፍ ለክልሉ ብሎም ለአገሪቱ እድገት ድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል፡፡ ወጣቱ ከሐሰተኛ ወሬዎች ራሱን በመጠበቅ ለክልሉ እድገትና ብልጽግና ድርሻውን መወጣት እንዳለበት የተናገረችው ደግሞ ሌላዋ ወጣት ኛዊች ቱት ናት፡፡ መንግሥትም ሰላምን በመደፍረስ የሕዝቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ በችግር ላይ የሚጥሉ አካላትን በማጣራት በተለይም ከልዩ ኃይል ጋር ተያይዞ ያለውን ጉዳይ በትኩረት ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቃለች፡፡ ወጣት ኡሞድ ኡታሊ በበኩሉ ወጣቱ በተለያዩ አሉቧልታዎች በመነሳት ድንጋይ ከመወርወር ይልቅ የተነሳውን ሀሳብ በውይይትና ተቀራርቦ በመነጋገር የሚፈታበትን ልምድ ማዳበር ይገባል ብሏል፡፡ በክልሉ ሰላም ለማስፈን የፀጥታ አካላት በተለይም በፖሊስና ልዩ ኃይል መካከል ያለው ግንኙነት መጠናከር አለበት ያለው ደግሞ ወጣት ሪያንግ ኮት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ህብረተሰቡ ወጀለኞችን አጋልጦ በመስጠትና መንግስትም ሕዝቡ የሚጠይቃቸውን ጥያቄዎች በተቻለ መጠን በወቅቱ ምላሽ መስጠት እንዳለበትም ጠይቋል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር  በሰጡት ምላሽ በወጣቱ ዘንድ የአንድነት፣ የአብሮነት፣ የመወያየትና መነጋገር ልምዶች ከዳበሩ ማናቸውንም ችግሮች በጋራ በማለፍ የክልሉን ህዝብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ ይቻላል ብለዋል፡፡ ይህን እውን ለማድረግ ሁሉም በጋራ መረባረብ እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ከልዩ ኃይል ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የተሃድሶ ስልጠና የሚወስዱበትን ሁኔታ ማመቻቸቱን አመልክተዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና ከከተማዋ ከአምስቱም ቀበሌዎች የተውጣጡ ወጣቶች ታድመውበታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም