በሚቀጥሉት አስር ቀናት ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች አንጻራዊ መጠናከር ያሳያሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት አስር ቀናት ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች አንጻራዊ መጠናከር ያሳያሉ
ሰኔ 25/2011 በሚቀጥሉት አስር ቀናት ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች አንጻራዊ መጠናከር የሚያሳዩ ሲሆን በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከባድ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ተገለጸ። የብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በሚቀጥሉት አስር ቀናት ዝናብ ሰጪ የአየር ሁኔታ ሲጠናከር በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ከባድ ዝናብ ይኖራል። በተለይ በምዕራብ አጋማሽ የኢትዮጵያ ስፍራዎች ላይ ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች አንጻራዊ ጥንካሬ ሊያሳዩ እንደሚችል የኤጀንሲው መረጃ ያሳያል። በዚህም መሰረት በኦሮሚያ ክልል በጅማ፣ ኢሉባቦር፣ ምስራቅና ምዕራብ ወለጋ፣ ሁሉም የሸዋ ዞኖች፣ ምዕራብና ምስራቅ ሀረርጌ፣ አርሲና ባሌ፣ አዲስ አበባ ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ ዝናብ እንዲሁም በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከባድ ዝናብ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህም በተጨማሪ ከአማራ ክልል ምዕራብና ምስራቅ ጎጃም፣ ሰሜንና ደቡብ ጎንደር፣ የባህርዳር ዙሪያ፣ አዊ፣ ሰሜን ሸዋና የትግራይ ክልል ሁሉም ዞኖች፣የጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ዞኖች ከመደበኛ ጋር የተቀራረብ ዝናብ እና በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከባድ ዝናብ ያገኛሉ ። ደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ህዝቦች ክልል የካፋ፣ ቤንች ማጂ፣ ጉራጌ፣ ሀዲያ፣ ወላይታ፣ ዳውሮ፣ ጋሞጎፋና ሲዳማ ዞኖች ከመደበኛ ጋር የተቀራረብ ዝናብ እና በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ከባድ ዝናብ ሊዘንብ ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ የሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ ድሬደዋ፣ ሀረር፣የአፋር ዞን 3 እና 5 እንዲሁም የሰገን ህዝቦች በጥቂት ስፍራዎቻቸው ላይ አነስተኛ ዝናብ ያገኛሉ። የተቀሩት የአገሪቱ አካባቢዎች ደረቃማ ሆነው እንደሚቆዩ ኤጀንሲው አመልክቷል። በመሆኑም በመኸር አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ያለው እርጥበት ስርጭት የክረምት ተጠቃሚ ለሆኑ አካባቢዎች ለዘር ምቹ እንደሚሆን ገልጸዋል። ከባድ ዝናብ ሊኖር ስለሚችል የተዘሩት ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ ተገልጿል። በተፋሰሶች አካባቢ ሲታይ አብዛኛው የአባይ፣ ባሮ አኮቦ፣ ተከዜ፣ ገናሌ፣ ዋቢሸበሌ፣ ኦሞ-ጊቤ ስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች ከመጠነኛ እርጥበት እስከ ከፍተኛ ዝናብ እንደሚያገኙ ይጠበቃል፤ የተቀሩት ደረቃማ ይሆናሉ።