ቀጥታ፡

መንግስት የህግ የበላይነት የማስከበር ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት አለበት-ተሳታፊዎች

ሰኔ 25/2011 መንግስት የህግ የበላይነትን የማስከበርና ህገ መንግስቱን የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በአግባቡ መወጣት አለበት ሲሉ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወጣጡ የውይይት ተሳታፊዎች ገለጹ። የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ ቴሌቪዥን በአገሪቷ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ሀሳባቸውን የገለጹት የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳነሱት መንግስት የህግ የበላይነት የማስከበሩን ተግባር በአግባቡ መወጣት አለበት ህብረተሰቡም ከመንግስት ጎን ሆኖ የአገሪቷ ሰላም ማረጋገጥ አለበት። የህግ የበላይነትን የሚፈታተኑ ተግባራት ሲከሰቱም መንግስት አፋጣኝ እርምጃ አስቀድሞ ቢወስድ ባላፈው ሳምንት የተከሰተው ድርጊት ዓይነት ወንጀል አይፈጠርም ነበር ሲሉ ገልጸዋል። የመንግስትን ስልጣን በኃይል የመያዝ ተግባር በዚህ ወቅት የማያስፈልግና ስልጣን መያዝ ካስፈለገም በህዝብ ይሁንታ በምርጫ ብቻ መሆን በሚገባው ጊዜ ላይ እንዲህ አይነት ድርጊት መፈጸሙ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል። አሁን የመጣውን ለውጥ ሁሉም የኢትዮጵያ ወንድም ህዝብ በጋራ በመሆን በከፍተኛ መስዕዋትነት ያመጡት በመሆኑም ለውጡን በመጠበቅ ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር ያስፈልጋል ብለዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ድግሪ ተማሪ የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ብዙአየሁ ደጋፋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ከአሁን በኋላ ለፖለቲካ ስልጣን ሲባል የአንድም ሰው ህይወት መጥፋት የለበትም ችግሮች ካሉ በውይይት መፍታት ያስፈልጋል። መንግስት የተለያዩ ሪፎርሞችን ቢያካሂድም ለዘመናት የተከማቹ ችግሮችን በአንድ ጊዜ መፍታት አይችልም ያሉት ረዳት ፕሮፈሰሩ፤ ችግሮቹ በሂደት ሊፈቱ ስለሚችሉም መታገስ ያስፈልጋል ብለዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም ካለፉ ታሪካችን በመማር ከልዩነት ይልቅ በአንድነት ላይ በመስራት በቀጣይ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ አለባቸው ብለዋል። በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ የተከሰተው ተግባር አገርን የሚያፈርስና በህዝቦች አንድነት ላይ አደጋ የሚያመጣ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በውይይቱ ላይ የተሳፉት የኦዲፒ ተወካይ አቶ ግዛቸው ገቢሳ ናቸው። የተከሰተው ችግር በኦሮሞ ህዝብና በኦሮሚያ ላይ እንደተከሰተ እንደሚወስዱና አጥብቀው የሚያወግዙት ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል። የኦፌኮ ተወካይ አቶ ደጀኔ ጣፋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ አሁን የምትከተለው ፌዴራላዊ ስርዓት የህዝቦች ራሳቸውን በራሳቸው የመስተዳደር ዕድል የሰጠ በመሆኑ ችግር ካለ በውይይት መፍታት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ከውይይት ውጭ ችግሮችን ለመፍታት መመካከር ዘመኑ የሚጠይቀው ጉዳይ በመሆኑም መንግስት ከምሁራን፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየት የአገሪቱን ችግር ለመፍታት መስራት አለበት ብለዋል። የህዝቦች አንድነት በመፈቃቀድ ላይ በተመሰረተ መልኩ አብሮነትንና አንድነትን ማጠናከር አንጂ በኃይል ለመጨፍለቅ የሚደረግ አካሄድ ከፍተኛ ጉዳት እንደሚያስከትልም ጠቁመዋል። ከኦሮሚያ ዐቃቤ ህግ ቢሮ የመጡት አሻማው ሰይፉ በበኩላቸው በአገሪቷ ህገ መንግስት ላይ በተቀመጠው መሰረትም ማንኛውም ቡድን ወይም የፖለቲካ ፓርቲ ስልጣን መያዝ ያለበት በምርጫ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል። ከምርጫ ውጭ ስልጣን ለመያዝ መመኮር ኢ-ህገመንግስታዊ ነው፣ተቀባይነትም የለውም ወደ ግጭት ከመግባት ባለፈ ፋይዳም የለውም ብለዋል። በመሆኑም መንግስት ህገ መንግስቱን ማስከበር አለበት ሲሉ ተናግረዋል አቶ ደጀኔ። በውይይቱም ከምሁራን፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣  ከወጣቶችና ከንግዱ ማህበረሰብ የተወጣጡ ሰዎች ተሳትፈውበታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም