የኢትዮጵያ የምግብና የመድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን በ42 የመጠጥ ምሽት ቤቶች ላይ እርምጃ ወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የምግብና የመድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን በ42 የመጠጥ ምሽት ቤቶች ላይ እርምጃ ወሰደ
ሰኔ 25/2011 የኢትዮጵያ የምግብና የመድሀኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ትንባሆና ሺሻ ሲያስጨሱ በተገኙ 42 የመጠጥ ምሽት ቤቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ። ባለስልጣኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር፣ ከፖሊስና ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ባደረገው ቁጥጥር ትንባሆና ሽሻ ሲያስጨሱ የነበሩ ምሽት ቤቶችን አግኝቷል። በቁጥጥር ወቅት በዚህ ህገ ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርትው ያገኛቸውን 42 የመጠጥ ምሽት ቤቶች ላይ ህጋዊ እርምጃ መወሰዱን አስታውቋል። በ2011 ዓ.ም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባፀደቀው የምግብና መድሃኒት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1112/2011 መሰረት ሲጋራና ሌሎች የትምባሆ ምርቶችን ማስጨስ መከልከሉ ይታወሳል። ክልከላው በተለይም ሆቴል፣ ሬስቶራንት፣ ምግብ ቤት፣ መጠጥ ቤቶች ላይ ከበር መልስ ባሉ ቦታዎች በ10 ሜትር ዙሪያ ማጨስ ይከለክላል። ሺሻን በተመለከተ፤ ምርቱን ወደ አገር ውስጥ ከማስገባት አንስቶ ማከፋፈል መሸጥ የማይቻል እንደሆነም ተደንግጓል። በህጉ መሰረት ይህንን ክልከላ ተላልፎ በተገኘ ላይ ከ3 ወር እስከ 5 ዓመት የሚደርስ እስራት እና ከብር አንድ ሺህ እስከ ሁለት መቶ ሺህ ብር ቅጣት ይጠብቀዋል። ህብረተሰቡ ትንባሆና ሺሻ የሚያስጨሱ አካላት ሲተያጋጥሙት በ8482 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ እንዲሰጥ ባለስልጣኑ ጥሪውን አስተላልፏል።